በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ወጣቶች እንዲሰጥ የተዘጋጁ ሸዶች ለባለሃብት መሰጠታቸው ቅሬታ ፈጠረ፡፡

ጥር ፲፪ ( አሥራ ሁለት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በባህርዳር ከተማ ጣና ክፍለ ከተማ ውስጥ ተገንብተው ለረዥም ጊዜ ያለ አገልግሎት ተቀምጠው የነበሩ ከ60 በላይ ሸዶች ለተደራጁ ስራ አጥ ወጣቶች እንዲሰጥ ቢወሰንም፣ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ጽህፈት ቤት ግን ሸዶችን ለባለሃብቶች በማከፋፈሉ ስርዓቱን ጠብቀው የተደራጁ ወጣቶች ከፍተኛ ቅሬታ እንዳደረባቸው ለክልሉ ዘጋቢ ተናገሩ፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎች እንደሚናገሩት በ2008 እና 2009 ዓም.ብቻ ተደራጅተው አቅም ላልፈጠሩ ወጣቶች ተሰጥቶ ከቤት ኪራይ ነጻ ሆነው ሃብት እንዲያፈሩ ቢታሰብም አሁን በተጨባጭ ወደ ሸዱ በመግባት እየተጠቀሙ ያሉት ግን ከፍተኛ ባለሃብቶችና ከጀመሩ ረጂም ዓመታት በስራው ላይ የቆዩ አምራቾች መሆናቸው ቅሬታ አሳድሮባቸዋል፡፡
ባለሃብቶች ከአሁን በፊት የነበራቸውን ነባር ፈቃድ በመተው በቤተሰቦቻቸው ስም አዲስ የሽርክና ማህበር ፈቃድ እንዲያወጡ ከተመቻቸ በኋላ ሸዱ መከፋፈሉ ፍትሃዊነት የጎደለው አሰራር መሆኑን ወጣቶች ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በሸዱ በመገልገል ላይ ያሉት ከፍተኛ ባለሃብቶች ለውሃ ማጠራቀሚያ አገልግሎት የሚውል የፋይበር ግላስ አምራቾችን ጨምሮ ልዩ ልዩ የሽንት ቤት መቀመጫና የአበባ ማስቀመጫ ዕቃዎችን የሚያመርቱ መሆናቸውን የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎች፤አንዳንድ ባለሃብቶች ቦታውን ከተረከቡ በኋላ ሸዱን ያለ አገልግሎት ዘግተው እንዳስቀመጡት አጋልጠዋል፡፡
ከከተማ አስተዳደሩ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ጽህፈት ቤት አመራሮች ጋር የጥቅም ግንኙነት የሌላቸው መሰፈርቱን ያሟሉ በርካታ የሽርክና ማህበራት አገልግሎቱን ለማግኘት በተደጋጋሚ ቢጠይቁም አዎንታዊ ምላሽ በማጣታቸው በክራይ ቤት ለተጨማሪ ወጭ እንደተዳረጉ ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ መድረኮች “ጥልቅ ተሃድሶ አድርገናል” በማለት የሚናገሩት የስርዓቱ አመራሮች ለወጣቱ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ እንደሆነ ቢናገሩም አሁንም ወጣቱን ከማገዝ ይልቅ ራሳቸው የሚጠቀሙበትን አሰራር በመዘርጋት ወደ ቀድሞ የሙስና ስራቸው እየተጓዙ በመሆኑ ከስርዓቱ ምንም ለውጥ እንደማይገኝ ቅሬታ አቅራቢዎች አስተያየታቸውን ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡