ኢሳት (ጥር 11 ፥ 2008)
ዳግም በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ረቡዕ በጥምቀት በዓል አከባበር ወቅትም በተለያዩ ቦታዎች ቀጥሎ መዋሉን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ከቀናት በፊት በምስራቅ ሃረርጌና በምስራቅ ወለጋ አካባቢዎች ሲካሄድ የሰነበተው ተቃውሞ አልባት አለማግኘቱንና የጸጥታ ሃይሎች በስፍራው እርምጃ መውሰድ መቀጠላቸውም ታውቋል።
የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት ትምህርት ያቋረጡ ዩኒቨርስቲዎች ትምህራትቸውን እንዲቀጥሉ ጥረታቸውን ቢቀጥሉም ተማሪዎች በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምክንያት ትምህርት አለመጀመሩን ለመረዳት ተችሏል።
ለእስር የተዳረጉ ተማሪዎች እንዲፈቱ ጥያቄ በማቅረብ ላይ ያሉት ተማሪዎች፣ የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች የሚወስዱትን የግድያ እርምጃ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።
በእለቱ የፀጥታ ሃይሎች የሚወስዱት የሃይል እርምጃ በመቀጠሉም ሟቾችንና ለእስር የተዳረጉ ሰዎችን በትክልል ማወቅ እንዳልተቻለ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ግለሰቦች ይገልጻሉ።
እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የሟቾች ቁጥር ከ150 በላይ መድረሱ ሲገለፅ መቆየቱ ይታወሳል።
ሁለተኛ ወርን ያለፈው ይኸው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ በአለም አቀፍ ደረጃ ትኩረትን ስቦ የሚገኝ ሲሆን የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ እንደሆነ አስታውቀዋል።