ኢሳት (ግንቦት 10 ፥ 2009)
በአማራ ክልል ለጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ከቀያቸው የተፈናቀሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ለአመታት ምትክ ቦታ አለማግኘታቸው ተገለጸ።
ለፋብሪካው ግንባታ ተብሎ ከመኖሪያ ይዞታቸው እንዲፈናቀሉ ከተደረጉት 213 አርሶ አደሮች መካከል 11 ዱ ብቻ ምትክ ቦታ እንደተሰጣቸው የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሃሙስ ዘግበዋል።
የስኳር ፋብሪካው ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በበኩሉ በፕሮጄክቱ ምክንያት ተፈናቅለው ካሳ ይገባቸዋል ከተባሉ ሁሉ ክፍያ ፈጽሜያለሁ ሲል ምላሽን ሰጥቷል።
ኮርፖሬሽኑ የካሳ ክፍያ መፈጸሙን ቢገልጽም ከቀያቸው ከተፈናቀሉት መካከል 213 አርሶ አደሮች መካከል 36ቱ ካሳ አልተከፈለንም በማለት ለህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ቅሬታን ማቅረባቸው ታውቋል።
በተቋሙ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ አስተዳደር ተወካይ የሆኑት አቶ ሃብታሙ ታደሰ በበኩላቸው ምትክ ቦታ ማግኘት ያለባቸው አርሶ አደሮች 213 ቢሆኑም እስከአሁን ድረስ ካሳ የተከፈላቸው 11 ብቻ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደር አጠቃቀም ቢሮ ምትክ ቦታ ያልተሰጣቸውን አርሶ አደሮች በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች በማደራጀት የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ይደረጋሉ ብለዋል።
አርሶ አደሮቹ ከእርሻ ይዞታቸው እንዲነሱ ተደርጎ የፋብሪካው ግንባታ ቢካሄድም የስኳር ፋብሪካው አጋጥሞታል በተባለ የሸንኮራ አገዳ እጥረት ምርት ማምረት ሳይችል መቅረቱን የክልሉ መንግስት በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ከጣና በለስ የስኳር ፋብሪካ በተጨማሪ ወደ አምስት የሚጠጉ ተመሳሳይ ፋብሪካዎች ግንባታቸው በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ለረጅም አመታት መስተጓጎሉ አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ከሁለት አመት በፊት ግንባታቸው ይጠናቀቃል ተብለው የተጠበቁት ፋብሪካዎች ሃገሪቱ ስኳር ላኪ ሃገር ያደርጓታል ተብለው ተስፋ እንደተጣለባቸው ሲገለጽ ቆይቷል።
ይሁንና የፋብሪካዎቹ ግንባታ መጓተት በመንግስት ላይ ካመጡት የፋይናንስ ኪሳራ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ስኳርን ከውጭ እንድታሰገባ ምክንያት መሆናቸውም ተመልክቷል።