(ሐምሌ– 5/2009)ከ50 ሺህ ሔክታር በላይ የሚሆነውን የጣና ሐይቅ በመሸፈን አደጋ የጋረጠው የእንቦጭ አረም የባህር ዳር ከተማን ጨምሮ በምዕራብ ጎጃም፣ ደቡብና ሰሜን ጎንደር ዞኖች የሚገኙ ህይወታቸውን ብርጣና ሐይቅ ከሚገኝ የምስኖ እና አሳ ምርት ያደረጉ ዜጎች ላይ መውደቃቸውን መረጃዎች አመላክተዋል። በተለይም የጣና ሐይቅ በሚያዋስናቸው ሰሜን ጎንደር፣ ጎርጎራ፣ አቼራ፣ ደንቢያ፣ ደንቢትና ማክሰኝት አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች በተስፋፋው አረም ምክንያት የአሳ ምርቱ በእለት ተእለት በማነሱ ከብቶቻቸው አረሙን ሲበሉ በመጫጫታቸው እና የውሃው መጠን እየቀነስ በመሄዱ ህይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁን ለማወቅ ተችሏል።
በዘርፉ ምርምር ያደረጉ ምሁር ለኢሳት እንደገለፁት ከሆነ በጣና ሐይቅ የተከሰተው ችግር አገራዊ ተደርጎ በመውሰድ አስቸኳይ ርብርብ ማድረግ ካልተቻለ የጣና ሐይቅ እንደ ሐረማያ ሐይቅ ሙሉ ለሙሉ የመድረቅ እጣ ፋንታ ሊያጋጥመው እንደሚችልና በሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች አካባቢያቸውን በመልቀቅ ለስደት እንደሚዳረጉ አስጠንቅቀዋል። ተመራማሪው አክለው እንደገለፁት ከሆነ የአዲስ አበባን ያህል ስፋት በሸፈነው የእንቦጭ አረም ምክንያት በሀይቁ ውስጥ ያለው አልሚ ምግብና ውሃ እየቀነሰ በመሄዱ አሳን ጨምሮ በውሃ ውስጥ የሚኖሩ ህይወት ያላቸው ፍጡራን የመጥፋት አደጋ አጋጥሟቸዋል።
ችግሩ ያሳሰባቸው ኢትዮጵያውያን ጉዳዩ አገራው አጀንዳ ተደርጎ እንዲውሰድ ቢጎተጉቱም በህወሓት የሚመራው መንግስት ትኩረት መስጠት አለመፈለጉ እንዳሳዘናቸው ተመራማሪው ለኢሳት ገልፀዋል።