ኢሳት (ታህሳስ 20 ፥ 2009)
በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት በጋምቤላ ክልል ስለተፈጸመ የመሬት አሰጣት ችግር ይፋ የተደረገው ጥናት ከእውነት የራቀና ሁሉንም ባለሃብቶች ያላሳተፈ ነው ሲሉ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ቅሬታ ማቀረባቸውን “ሪፖርተር” ዘገበ።
በክልሉ በእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ እነዚሁ ባለሃብቶች ሰሞኑን የቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ ባለሃብቱን ያላሳተፈ፣ ከእውነት የራቀ እና የስራ አፈጻጸሙን በጅምላ የተቸ ነው ማለታቸውን በዘገባው ተመልክቷል።
በጋምቤላ ክልል በሃጋዊ መንገድ መሬት ተረክበው ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ ወደ ስራ መግባታቸውን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይናግራሉ።
ባለሃብቶቹ የወሰዱትን ብድር እና የቀረጥ ነጻ መብታችውን ለሌላ አላማ ያዋሉ ተለይተው ዕርምጃ ሊወስድባቸው ይገባል እንጂ ሁሉንም ባለሃብት በአንድ ላይ ጥፋተኛ ብሎ መፈረጅ አይገባም ሲሉ አመልክተዋል።
በክልሉ ስለተፈጸሙ ብልሹ የመሬት አሰጣጦችና የገንዘብ ኪሳራዎች ዙሪያ ጥናቱን ያቀረበው የባለሙያዎች ቡድን በጋምቤላ ክልል የተካሄደው የመሬት መስጠት ሂደት ውጤት ያላመጣና ደካማ እንደነበር ማስታወቁ ይታወሳል።
በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ልዩ ትዕዛዝ የተካሄደው ይኸው ጥናት በአንድ የመሬት ይዞታ ላይ ተመሳሳይ ብድር ሲሰጥ በመቆየቱ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ኪሳራ መድረሱን ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ100 ለሚበልጡ ባለሃብቶች ሲሰጡ የነበረው ብድር የገባበት አለመታወቁና በርካታ ባለሃብቶችም በአካል የሌሉ መሆናቸውን ጥናቱ ይፋ አድርጓል።
ቁጥራቸው ያልተገለጸ የህንድ ባለሃብቶች ደግሞ ከመንግስት የወሰዱትን ብድር ሳይመልሱ ከሃገር መኮብለላቸው ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ሚኒስቴር በበኩሉ የወሰዱትን ብድር ሳያወራርዱ ከሃገር በወጡ የህንድ ባለሃብቶች ላይ ህጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ ቢገልፅም ባለሃብቶች ምን ያህል ብር ከመንግስት እንደወሰዱ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።
በጋምቤላ ክልል ከ600 በላይ ባለሃብቶች ከ630 ሄክታር መሬት በላይ ለኢንቨስትመንት ቢሰጣቸውም መልማት የቻለው ግን ወደ 15 በመቶ ብቻ መሆኑን ሰሞኑን ይፋ የተደርገው ጥናት አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የንግድ ባንክ ለባለሃብቶቹ ወደ 5 ቢሊዮን ብር አካባቢ ብድር ሰጥተው የነበረ ሲሆን፣ ብድሩን የወሰዱት አብዛኞቹ ባለሃብቶች ገንዘቡን እንደያዙ መሰወራቸውን ከጥናቱ ለመረዳት ተችሏል።
ጥናቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ሁለት የቱርክ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ባለሃብቶች በተመሳሳይ መልኩ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር አካባቢ የሚጠጋ የመንግስት ብድር ሳያወራርዱ ከሃገር መኮብለላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
በጋምቤላ ከተሰማሩ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ከ75 በመቶ በላይ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው ሲገለጽ ቆይቷል። 200 ሰዎች የወሰዱት 4.9 ቢሊዮን ብር መባከኑም በጥናቱ ይፋ ሆኗል።