(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 10/2010) በጎጂና በጊዲዮ ብሔረሰብ መሀል የተፈጠረው ግጭት ቀጥሎ ትላንት 6 ህጻናትን ጨምሮ 11 ሰዎች መገደላቸው ታወቀ።
የተሰደዱ ሰዎችም ወደ 100 ሺህ መጠጋቱ እየተነገረ ነው።
በበጉጂ ዞን በሚኖሩ የጌዲዮ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እንዲቆም በሰሜን አሜሪካ የጌዲዮ ማህበረሰብ አባላት ጠይቀዋል።
አባላቱ ለኢሳት በላኩት መግለጫ ላይ እንደገለጹት ለዘመናት በጋራ ተከባብረው ተዋልደውና ቤተሰብ ሆነው በኖሩ የሁለቱ ብሔረሰቦች መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠረው ግጭት ከ100 በላይ ሰዎችን ህይወት ማጥፋቱም ታውቋል።
ግጭቱ ከፍተኛ ሰብዓዊ ዕልቂት እያስከተለ ባለበት በዚህን ወቅት በሀገር ቤት የሚሰራጩ መገናኛ ብዙሃን ስለሁኔታው አለማንሳታቸው ተገልጿል።
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የተቀሰቀሰው ግጭት መብረድ አልቻለም።
በትላንትናው ዕለት ብቻ 11 ሰዎች መገደላቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ከተገደሉት መሃል ስድስቱ ህጻናት መሆናቸው ታውቋል።
በምዕራብ ጉጂ የተከሰተውና ሁለተኛሳምንቱን የያዘው ግጭት ከ100 በላይ ሰዎችን ማጥፋቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የጌዲዮ ተወላጆች ማህበረሰብ ለኢሳት በላከው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ከጌዲዮ ብሄረሰብ ብቻ 75 ሰዎች ተገድለዋል። 100ሺህ የሚሆኑት ተሰደው በየመጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ።
ግድያው በስለት ጭምር የሚካሄድ በመሆኑ አሰቃቂ ነው ያሉት የማህበረሰቡ አባላት ለሁለት ሳምንት የዘለቀውን ግጭት ለማብረድ አለመሞከሩ ሁኔታውን አስደንጋጭ ያደርገዋል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት 10 ቀናት በምዕራብ ጉጂ ቀርጫ በሚባል ወረዳ ቃርጫ ከተማ፣ ብርብርሳ ቤራ፣ ኤዴራ፣ ኤልፋርዳ፣ ቢሊዳ፣ ዲንቱ፣ ዲቢሳና ሶኬ በተባሉ አካባቢዎች በሚኖሩ የጌዲዮ ብሄረሰቦች ላይ የተፈጸመው ጥቃት መጠነ ሰፊ በመሆኑ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከተጠቀሰው ሊጨምር እንደሚችል እየተነገረ ነው።
በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የጌዲዮ ብሄረሰብ አባላት ባወጡት መግለጫ ላይ እንደተገለጸው በጥቃቱ ከወደሙት ንብረቶች በተጨማሪ ሶስት አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል።
ቀዬ መንደራቸውን ትተው የተሰደዱ የጌዲዮ ተወላጆች በዲላ፡ በይርጋጨፌ በገደብና በወናጎ ወረዳ ከተሞች በተዘጋጁ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ሰፍረው እንደሚገኙ ተገልጿል።
የተፈናቃዩ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በአሁኑ ጌዜ ከመጠለያ ጣቢያዎቹ ውጪ ሜዳ ላይ ተበትነው እንደሚገኙ የጠቁሱት የጌዲዮ ተወላጆች በአከባቢው ከባድ ዝናብ ከመጣሉ ጋር ተያይዞ የተፈናቀለው ህዝብ ለህይወት አስጊ በሆኑ ችግር ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል።
ግጭቱ ከተከሰተ ሁለተኛ ምንቱን የያዘ ቢሆንም እስከአሁን በክልል መንግስታትም ይሁን በፌደራል መንግስቱ ትኩረት እንዳጣ ተወላጆቹ ባወጡት መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።
ግጭቶቹ በተከሰተባቸው አከባቢዎች የመከላከያና የኮማንድ ፖስት ወታደሮች የሚገኙ ቢሆንም አንዳችም እርምጃ አለመውሰዳቸው ጉዳዩን አሳሳቢ ያድርገዋል ያሉት በሰሜን አሜሪካ የጌዲዮ ተወላጆች ማህበረሰብ አባላት ሁለቱን ወንድማማች ብሄረሰቦች ለማጋጨት የተጎነጎነ ሴራ ለመኖሩ አመላካች እንደሆነ ገልጸዋል።
የክልልም ሆኑ የብሄራዊ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያዎች ከ100 ሺህ በላይ የተፈናቀሉበትን ግጭት በተመለከተ አንዳችም ሽፋን መስጠት አለመፈለጋቸውንም በመጥቀስ የኢትዮጵያ ህዝብ የመጣውን አደጋ በቅርበት እንዲከታተለው ጠይቀዋል።
በየመጠለያ ጣቢዎቹ ለሚገኙት ወገኖቹም ድጋፍ እንዲያደርግ በሰሜን አሜሪካ የጌዲዮ ተወላጆች ማህበረሰብ አባላት ጥሪ አድርገዋል።