በጎንደር ዳባት 40 የሚሆኑ ሰዎች መታሰራቸው ተነገረ

ኢሳት (ሰኔ 6 ፥ 2008)

ባለፈው ሳምንት በሰሜን ጎንደር ዳባት ከተማ ከኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ማሽን መነሳት ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ወደ 40 የሚደርሱ ነዋሪዎች ለእስር ተዳረጉ።

የዞኑ አስተዳደሮች ከአካባቢው ነዋሪ ጋር ድርድር እንዲካሄድ ጥረትን ቢያደርጉም የከተማዋ ነዋሪዎች ለእስር የተዳረጉ ሰዎች ከእስር እንዲለቀቁ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጣቸውን እማኞች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

የተቀሰቀሰው ግጭት ለሁለተኛ ሳምንት ዕልባት አለማግኘቱን የተናገሩት ነዋሪዎች የጸጥታ ሃይሎች የሚፈለጉ ሰዎች አሉ በማለት በከተማዋ አሰሳን እያካሄዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

በከተማዋ ትምህርት ቤቶችና የመንግስት ተቋማት ዝግ ሆነው የቀጠሉ ሲሆን፣ በርካታ የጸጥታ ሃይሎች ሰፍረው እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።

የክልሉና ሌሎች የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በከተማው የተቀሰቀሰን ተቃውሞ ከዘረፋ ጋር የተገናኘ አስመስሎ ለማቅረብ በከተማዋ ቀረጻን እያካሄዱ መሆኑን እማኞች አክለው ገልጸዋል።

የደባርቅ ከተማን ጨምሮ ሌሎች የዞን ከተሞች ከዳባት ነዋሪ ጎን በመቆም አጋርነታቸውን እያሳዩ እንደሆነ ከነዋሪዎቹ ጋር ከተደረገው ቃለምልልስ ለመረዳት ተችሏል።

ባለፈው ሳምንት የከተማዋ ነዋሪ ወደ 25 አመት ገደማ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ የኤለክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ማሽን (ትራንስፎርመር) ወደ መቀሌ ሊወሰድ ነው በማለት ማሽኑን ከተሽከርካሪው ላይ በማውረድ ተሽከርካሪዎች በእሳት ማጋየታቸው ይታወሳል።

የከተማዋ ነዋሪው ያነሳውን ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎ በዳባት ከተማ ውጥረት የነገሰ ሲሆን፣ ጉዳዩን በድርድር ለመፍታት የተደረገ ጥረት ሊሳካ አለመቻሉን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።

በከተማዋ ተባብሶ የቀጠለውን ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎ ከቀናት በፊት የከተማ አስተዳዳሪዎች ወደጎንደር ከተማ መሰደዳቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው።