ኢሳት (ጥር 12: 2009)
በጎንደር የጥምቀት በዓል ከመቼውም ባነሰ ሁኔታ በተቀዛቀዘ ሁኔታ መከበሩን የአይን እማኞች ገለጹ።
እማኝነታቸውን ለኢሳት የገለጹት አንድ የጎንደር ከተማ ነዋሪ፣ ህዝቡ አደባባይ ከመውጣት ተቆጥቦ በአብዛኛው በቤቱ መዋሉን አስታውቀዋል።
ይህም ሆኖ ግን ከተለያዩ ወረዳዎችና አካባቢዎች አበል እየተከፈለ በርካታ ቄሶችን ጨምሮ በተለያዩ ደረጃ የሚገኙ ካድሬዎች ወደ ጎንደር እንዲሄዱ በማድረግ በዓሉን በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ጥረት መደረጉ ተገልጿል።
በከፍተኛ የጸጥታ ቁጥጥር በጎንደር በተከበረው የጥምቀት በዓል ከዚህ በፊት በከፍተኛ ቁጥር ይገኙ የነበሩ የውጭ ሃገር ጎብኚዎች አለመገኘታቸውን የአይን እማኙ ለኢሳት ገልጿል።
ህብረተሰቡ አደባባይ ወጥቶ ለማክበር ያልፈለገበት ምክንያት በርካታ ሰዎች በተገደሉበትና በታሰሩበት ሁኔታ ደስታችንን መግለፅ አንችልም በሚል መሆኑን የጎንደር ከተማ ነዋሪ ተናግረዋል።
አርብ ዕለት በጎንደር የሚካዔል ታቦት የሚገባበትና በደማቅ ሁኔታ የሚከበር ቢሆንም፣ በተቀዛቀዘ ሁኔታ መካሄዱንም ለማወቅ ተችሏል።
በአንዳንድ ቦታዎችም ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ሰራተኛ በመሰማራቱ ከፍተኛ ግርግር እንደነበረም ተገልጿል።
እንደነዋሪው ገለጻ በጎንደር በተከበረው የጥምቀት በዓል ከከተማው ነዋሪዎች ይልቅ ከሌላ ቦታ እንዲመጡ የተደረጉ ሰዎች የተሞላ እንደነበር ተናግሯል።