ኢሳት (ሃምሌ 11 ፥ 2008)
የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በጎንደር በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ የተገደሉት የመንግስት ታጣቂዎች 11 መሆናቸውን የብሄራዊ መረጃና ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ። የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎች ደግሞ 5 መሆናቸውንም አስታውቋል። ግጭቱ ከጎንደር ባሻገር በሌሎች አካባቢዎች መዛመቱንና ግጭት መከተሉንም አረጋግጧል።
የብሄራዊ መረጃና ፌዴራል ፖሊስ የጸረ-ሽብር ግብረ ሃይል እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫ ተጠርጣሪ የተባሉ ግለሰቦችን ለመያዝ የመንግስት ሃይሎች በተንቀሳቀሱበት ወቅት በተከፈተባቸው ተኩስ 9 የፌዴራል ፖሊስ አባላት አንድ የአማራ ክልል ፖሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት አባል መገደላቸውን አስታውቋል።
ከዚህ ተጨማሪ 11 የፌዴራል ፖሊስ አባላት መቁሰላቸውን በመግለጫው የተመለከተ ሲሆን፣ 5 የክልል ፖሊሶች እንደቆሰሉ ይፋ ሆኗል።
በሆቴሎች፣ በባንኮችና፣ በሌሎች ተቋማት ላይም ጉዳት እንደደረሰ የተገለጸ ሲሆን፣ 2 የፌዴራል ፖሊስ መኪኖች መቃጠላቸውን፣ አንድ የጎንደር ዩኒቨርስቲ አምቡላንስ መሰባበሩም በመግለጫው ተዘርዝሯል።
በአጠቃላይ 27 የፌዴራል ፖሊስ፣ የመከላከያና የክልል ፖሊሶች ለተገለገሉበትና ለቆሙበት ድርጊት መቀመጫቸውን በኤርትራ ያደረጉ ሃይሎችና የኤርትራ መንግስት ድጋፍ አድርገዋል ሲልም መግለጫው ተጠያቂ አድርጓቸዋል።
መግለጫው በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ 5 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።