ኢሳት (ሃምሌ 20 ፥ 2008)
በቅርቡ በማራ ክልል በጎንደር ከተማ በነዋርዎች ዘንድ የተነሳው “የነጻነትና የማንነት” ጥያቄ ከሽብርተኛ ድርጊት ጋር የያያያዙ የመንግስት አካላት ይቅርታን እንዲጠይቁ የከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።
በክልሉ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ሰሞኑን የክልሉና የብአዴን ሃላቺዎች ከነዋሪዎች ጋር ምክክርን ለማካሄድ በጠሩት ልዩ ስብሰባ ላይ ነዋሪዎች የተሰማቸውን ቅሬታ እንዳቀረቡ በስብሰባው የተሳተፉ እማኞች ለኢሳት አስታውቀዋል።
የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳና፣ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በነዋሪው የቀረበን ጥያቄ ከሽብርተኛ ድርጊት ጋር አመሳስለው ማቅረባቸው በነዋሪዎቹ ዘንድ ተጨማሪ ቁጣን እንዲቀሰቅስና በስብሰባው ወቅት አጀንዳ ሆኖ መቅረቡ ታውቋል።
በዚሁ ስብሰባ ላይ የታደሙ የከተማዋ ነዋሪዎች ተቃውሞን ከሽብርተኛ ድርጊት ጋር አያይዘው ያቀረቡ አካላት በይፋ ይቅርታን እንዲጠይቁ አበክረው መጠየቃቸውን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የስብሰባው ተሳታፊዎች አስረድተዋል።
አቶ በረከት ስምዖን፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ ሌሎች የብዓዴን አባላት ተሳታፊ በነበሩት በዚሁ ልዩ ህዝባዊ ስብሰባ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በህዝቡ የተነሳው የነጻነትና የማንነት ጥያቄ ህጋዊ ምላሽን እንዲያገኝ መጠየቃቸውም ታውቋል።
የብአዴን አመራሮች ከነዋሪው የቀረበን ጥያቄ አግባብነት ያለው ነው በማለት በቀላሉ ለማለፍ ቢሞክሩም ነዋሪዎች አመራሮቹ የሚያደርጉት ንግግር በማቋረጥ ተቃውሞ ሲያሰሙ መዋላቸውን እማኞች አክለው አስረድተዋል።
ብአዴን ተላላኪ ድርጅት ነው በማለት የሰላ ትችትን አቅርበዋል የተባሉ የከተማዋ ነዋሪዎች በክልሉ የሚነሱ ህዝባዊ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ አበክረው መጠየቃቸውንም በስብሰባው የታደሙ ምንጮች ለኢሳት አስታውሰዋል።
በቅርቡ በጎንደር ከተማ የወልቃይት ኮሚቴ አባላትን ለመያዝ የተደረገ ጥረት በነዋሪው ዘንድ ተቃውሞን ቀስቅሶ ከአምስት በላይ የፖሊስ አባላት መገደላቸው ይታወቃል።
በነዋሪው ዘንግ የተቀሰቀሰውን ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎ ከፍተኛ የብዓዴን አመራሮች የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችን ሲያወያዩ መቆየታቸው ታውቋል።