ኢሳት (ሃምሌ 11 ፥ 2008)
በቅርቡ በጎንደር ከተማና አካባቢው ከማንነት ጥያቄ ጋር የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ መንግስት በሽብርተኛ ድርጊት መፈረጁ በነዋሪው ዘንድ ተቃውሞ ማስነሳቱን የአርማጭሆ ነዋሪዎች ለኢሳት ገለጡ።
በአካባቢው አሁንም ድረስ ውጥረት መኖሩን የተናገሩት ነዋሪዎች ህዝቡ ዘርን ሳይለይ በአንድነት በመሆን መብቱን ለማስከበር ጥረት እያደረገ መሆኑን ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት ተቀስቅሶ የነበረውን ግጭት ከሽብርተኛ ድርጊት ጋር ማገናኘታቸው ህዝቡ መንግስት 25 አመት ሙሉ ውሸት ነው ሲነግረን የቆየው የሚል ሃሳብ እንዲይዝ አድርጎታል ሲሉ ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል።
ሁሉንም ነገር ተረድተን በተጠንቀቅ ላይ እንገኛለን የሚሉት የአርማጭሆ ነዋሪዎች በከተማና በገጠር ያሉ ነዋሪዎች የጀመሩትን የማንነት ጥያቄ ለማስከበር የዘር ማንነት ለማስወገድ በአንድነት እየታገሉ እንደሚገኙ በሰጡት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
የማንነት ጥያቄው ከዘር ግጭት ጋር አይገኛኝም ሲሉ የገለጹት ነዋሪዎች ህዝቡ ቁጣውን እየገለጸ ያለው አስተዳደራዊ በደል በፈጸሙ አካላት ላይ ብቻ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል።
ከቀናት በፊት በጎንደር ከተማ ተቀስቅሶ የነበረውን የማንነት ጥያቄ መንግስት ከሽብርተኛ ድርጊት ጋር የተገናኘ እንደሆነ በመግልጽ እርምጃ መውሰዱን ማስታወቁ ይታወሳል።
ይሁንና የማንነት ጥያቄን እያቀረበን እንገኛለን የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች ያቀረቡት ህጋዊ የማንነት ጥያቄ ምላሽን እስኪያገኝ ድረስ ትግላቸው ቀጣይ መሆኑን አክለው አስታቀዋል።