በጎንደር የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ

ኢሳት (ሃምሌ 8 ፥ 2008)

ከቀናት በፊት በጎንደር ከተማ ተቀስቅሶ ከነበረው ህዝባዊ አመጽ ጋር በተገናኘ በትንሹ 10 ሰዎች መገደላቸውና ድርጊቱ በከተማ ውጥረት ማንገሱን አለም-አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አርብ ዘገቡ።

በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ድርጊቶች በበርካታ የሃገሪቱ አካባቢዎች ሲካሄዱ መሰንበቱን ያወሳው አልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ የቱሪስቶች መስሕብ የሆነችው ጎንደር ከተማ ያልተለመደ የስጋት ድባብ እንደሚታይበት በግጭቱ ዙሪያ ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።

በጎንደር በተቀሰቀሰው ግጭት ፖሊሶችን ጨምሮ 10 ሰዎች መገደላቸውንም አልጀዚራ ከኳታር ዶሃ የራሱን ምንጮች ጠቅሶ ባቀረበው ዘገባ የሟቾቹ ቁጥር በትንሹ 10 መድረሱን ገልጿል።

ሆኖም መንግስት 5 ፖሊሶችና አንድ ሲቪል ብቻ መገደላቸውን ቢገልጽም፣ በሌላ ወገን በከተማዋ የሚኖሩ አክቲቪስቶች የሟቾቹ ቁጥር በትንሹ 20 መድረሱን እንደተናገሩም በዘገባው አስፍሯል።

የግጭቱ መነሻ የወልቃይትን ህዝብ የማንነት ጥያቄ የሚያቀነቅኑ ሰዎች ለመያዝ በተሞከረበት እንደሆነ የገለጸው አልጀዚራ ወልቃይቶች በግድ በትግራይ ክልል ውስጥ እንድንካለል ተደርገናል በሚል ተቃውሞ እንደሚያሰሙ በዘገባው አስታውሷል። የመብት ጠያቂዎች በአማራ ክልል መካለል እየፈለጉ በመንግስት በኩል ፈቃደኛነት አለመኖሩንም አስፍረዋል።

በወልቃይት ሆነ በአማራ የተቃውሞ ሃይላት የሃገሪቱ የፖለቲካ አመራር በትግራዮች ተፅዕኖ ስር ይገኛል ማለታቸውን የጠቀሰው አልጀዚራ፣ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል 300 ሰዎች የተገደሉበት ተቃውሞ እንደነበርም በዘገባው አስታውሷል።

ሶማሊላንድ ፕሬስ የተሰኘ መገናኛ ብዙሃን በበኩሉ እስከ 20 የሚደርሱ ሰዎች በግጭቱ መሞታቸውን የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ አርብ ለንባብ ባበቃው እትሙ አስፍሯል።

በጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰው ይኸው ህዝባዊ ተቃውሞ እልባትን እንዲያገኝ የመንግስት ተወካዮች ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ምክክር በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ጋዜጣው እማኞችን በመጥቀስ አስነብቧል።

ከቀናት በፊት ከትግራይ ክልል ወጥተዋል የተባሉ የደህንነት አባላት የወልቃይት ጠገዴ የኮሚቴ አባልን ለመያዝ ጥረት ባደረጉ ጊዜ የከተማዋ ነዋሪ ድርጊቱን በመቃወም ግጭት መቀስቀሱ ይታወሳል።

በጎንደር ከተማና በአጎራባች አካባቢዎች የተዛመተውን ይህንኑ ግጭት ተከትሎ አሜሪካንን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት ዜጎቻቸውን ወደ ስፍራው በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ጥንቃቄን እንዲያደርጉ አሳስበው ይገኛል።

የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት በጸረ-ሰላም ሃይሎች የተጠነሰሰ ነው ሲሉ የገለጹ ሲሆን፣ በግጭቱ ስለሞቱ ሰዎች ቁጥር ማረጋገጫን ከመስጠት መቆጠባቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።