በጎንደር የስራ ማቆም አድማው ለ3ኛ ቀን ቀጥሎ ዋለ
(ኢሳት ዜና የካቲት 14 ቀን 2010 ዓ/ም) በአማራ ክልል የተጠራውን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ የጎንደር ከተማ ህዝብ አድማውን ለ3ኛ ቀን ሲያካሂድ ውሎአል። ከፍተና ቁጥር ያላቸው ወታደሮች በከተማዋ እየተንቀሳቀሱ የስነ ልቦና ጫና ለመፍጠር ሙከራ ቢያደርጉም፣ ነጋዴዎች በአቋማቸው በመጽናት የመጨረሻውን ቀን የአድማ ጥሪ ተግባራዊ አድርገዋል። አድማውን አስተባብረዋል የተባሉ አንዳንድ ወጣቶች መታሰራቸው ታውቋል።
በባህርዳር ከተማ ደግሞ ነጋዴዎች ድርጅቶቻቸውን በሃይል እንዲከፍቱ ተገደዋል። ብዙዎቹ ነጋዴዎች ማስፈራሪያውን ባለመቀበል በአድማው በመቀጠላቸው የንግድ ድርጅቶቻቸው ታሽጎባቸዋል። የታሸጉት የንግድ ድርጅቶች አለመከፈታቸውንም ወኪላችን ገልጿል። ባለፈው ሰኞ አድማው ከጎንደርና ከባህርዳር በተጨማሪ በደብረታቦርና ሌሎች የምዕራብና የምስራቅ ጎጃም ከተሞች ሲካሄድ ነበር። በክልሉ ውስጥ የሚታየው የመረጃ አፈና መጠናከር ህዝቡ መረጃዎችን በፍጥነት እንዳይለዋወጥ አግዶታል። ይህም ሆኖ በእነዚህ ከተሞች የተሳካ ተቃውሞ ማካሄድ ተችሎአል።
የስራ ማቆም አድማው የተጠራው የታሰሩት ዜጎች እንዲፈቱ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ እና ህዝብ ያነሳቸው መብቶች ምላሽ እንዲያገኙ ለመጠየቅ ነው።