ኢሳት (ጥቅምት 8 ፥ 2009)
በጎንደር ከተማ ለሁለተኛ ቀን የቀጠለው የስራ ማቆም አድማ ለማስቆም የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ዕርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጡ። የክልሉ መንግስት ሰኞ ረፋድ ጀምሮ በከተማዋ የሚገኙ በርካታ የንግድ ተቋማት መዘጋታቸውን ቢያረጋግጥም አድማው ግን ከሽፏል ሲል ማስታወቁ ይታወሳል።
ይሁንና የከተማዋ ነዋሪዎች ቁጥሩ ከፍተኛ የሆን የጸጥታ ሃይል በከተማው ዋና ዋና የንግድ ስፍራዎች አካባቢ በመሰማራት የተዘጉ የንግድ ድርጅቶች እንዲከፍቱ ግፊት እያደረጉ መሆኑ ታውቋል።
በሃገሪቱ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና በተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄዱ ያሉ የሃይል ዕርምጃዎችን በመቃወም የከተማዋ ነዋሪ ከሰኞ ጀምሮ ለሶስት ቀን የሚቆይ የስራ ማቆም አድማ መጀመራቸው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
ከተማዋ አለመረጋጋት ውስጥ መሆኗን የሚናገሩት ነዋሪዎች የጎንደር ከተማ አስተዳደርና የንግድ ቢሮ በአድማው ተሳታፊ በሆኑ ተቋማት ላይ የማያዳግም ዕርምጃ ይወስዳሉ ሲሉ በማስፈራራት ላይ መሆናቸውን ዕማኞች አስረድተዋል።
በሃምሌ ወር በባህር ዳር እና ጎንደር ከተሞች የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ሁለቱ ከተሞች ተደጋጋሚ የስራ ማቆምና ከቤት ያለመውጣት አድማ ሲያካሄዱ መቆየታቸው ይታወቃል።
ይሁንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባሪ ከተደረገ በኋላ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች አድማ ሲያካሄዱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፣ የከተማዋ አስተዳደር ሁሉም የንግድ ተቋማት ስራቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቋል።