በጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጸረ-ሰላም በሆኑ የውጭ ሃይሎች የተቀነባበረ ነው ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ

ኢሳት (ሃምሌ 8 ፥ 2008)

የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ከቀናት በፊት በጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጸረ-ሰላም በሆኑ የውጭ ሃይሎች የተቀነባበረ ነው ሲሉ አርብ ለመገኛኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ከግጭቱ ጋር በተገናኘ ስለደረሰው ጉዳት መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡት ሚኒስትሩ የውጭ ሃይሎች ያሏቸውን አካላት በስም ያልጠቀሱ ሲሆን፣ ድርጊቱ ኢትዮጵያን የማተራመስ ተልዕኮ ነበረው ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ተጠርጣሪ የተባሉ አካላትን ለመያዝ ጥረት ቢያደጉም፣ የታጠቁ አካላት በወሰዱት ዕርምጃ ጉዳት መድረሱን የመንግስት ቃል-አቀባዩ ለመገኛኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

ስድስት ተፈላጊ የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ጥረት ቢያደርግም በተነሳት ተቃውሞ ምክንያት ተፈላጊ የተባሉት ሳይያዙ መቅረታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ መንግስት ተፈላጊዎችን ለመያዝ እርምጃ እወስዳለሁ ሲል አክሎ አመልክቷል።