ኢሳት (ጥቅምት 7 ፥ 2009)
የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመቃወም ለሶስት ቀን የሚቆይ የስራ ማቆም አድማ ሰኞ ጀመሩ።
የከተማዋ ነዋሪዎች የወሰዱትን ዕርምጃ ተከትሎ በከተማዋ የሚገኙ በርካታ የንግድ ተቋማት በስራ ማቆሙ አድማ ተሳታፊ መሆናቸውን ከዜና ክፍላችን ጋር ቃለ-ምልልስን ያደረጉ ነዋሪዎች አስረድተዋል።
ለሶስት ቀን የሚቆየው ይኸው አድማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከመቃወም በተጨማሪ በቅርቡ በቢሾፍቱ ከተማ ከእሬቻ በዓል አከባባር ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች አጋርነትን ለማሳየት ያለመ እንደሆነ መረዳት ተችሏል።
የከተማዋ ነዋሪዎች ሰኞ ረፋድ አድማውን በጀመሩ ጊዜ የጸጥታ ሃይልች የንግድ ተቋማትን እንዲከፍቱ ግፊትን ቢያደርጉም ነዋሪው በእምቢተኝነቱ መጽናቱን እማኞች አስታውቀዋል።
በሃምሌ ወር በጎንደርና በባህር ዳር ከተሞች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ ሰዎችን ድርጊት በማውገዝ በየከተሞቹ ተደጋጋሚ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ሲካሄዱ መቆየታቸው ይታወሳል።
ይሁንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ለሶስት ቀን የሚቆይ የስራ ማቆም አድማ ሊያካሄዱ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።
አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ቢሆንም ሁሉም ነገር የተከለከለ ነበር ሲሉ የገለጹት ነዋሪዎች፣ ነዋሪው የጀመረውን ትግል ለመቀጠል ቁርጠኝነትን እያሳየ እንደሚገኝ አክለው ገልጸዋል።
በሳምንቱ መገባደጃ ቅዳሜ በዝርዝር የተገለጸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲህ ያሉ አድማዎችን የሚከለክል ቢሆንም፣ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች አዋጁን በግልፅ በመቃወም አድማውን ለመጀመር እንደወሰዱ ለኢሳት ቃለምልልስን የሰጡ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ለአራተኛ ጊዜ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ባለው በዚሁ የስራ ማቆም አድማ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ አብዛኞቹ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መስተጓጎላቸውን እማኞች አስረድተዋል።
የክልሉ መንግስት በበኩሉ የስራ ማቆም አድማ መጀመሩን አረጋግጦ ድርጊቱ ከሰዓታት ቆይታ በኋላ ሊከሽፍ ችሏል ሲል ሰኞ ምሽት ገልጿል። ሆኖም የስራ ማቆም አድማው ተጠናክሮ መቀጠሉን እማኞች ከስፍራው ተናግረዋል።