ኢሳት (የካቲት 27 ፥ 2009)
በጎንደር ከተማ ከንቲባ መኖሪያ ቤት ላይ የቦንብ ጥቃት ተፈጸመ። ጥቃቱን የፈጸመው አካል ማንነት አልታወቀም። በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች በጥርጣሪ ተሰብሰብው ታስረዋል።
በሰሜን ጎንደር ዞን የጎንደር ከተማ ከንቲባ የሆኑት አቶ ተቀባ ተባባል መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው ቅዳሜ ሌሊት 10 ሰዓት ላይ መሆኑን የገለጹት ምንጮች በጥቃቱ በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱን አመልክተዋል።
ቅዳሜ ለዕሁድ አጥቢያ ከሌሊቱ 10 ሰዓት በከንቲባው በአቶ ተቀባ ተባባል መኖሪያ ቤት ላይ በደረሰው ጥቃት በሰው ላይ ጉዳት ባይደርስም፣ አንድ ሰርቪስ ቤት መውደሙን የአይን ምስክሮች ገልጸዋል። ጥቃቱ በመንግስት አካላት ላይ ድንጋጤ በመፍጠሩ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ በመግባት ዕሁድ የቤት ለቤት አሰሳ አድርገዋል።
የአርበኞች ግንቦት 7 ታጣቂዎች ገብተዋል በሚልም መንገዶች ጭምር ተዘግተው በመኪኖች ላይ ፈተሻ መደረጉም ታውቋል።
በጠገዴ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ተራ ሰራተኛነት በኋላም ከሰሜን ጎንደር ግብርና መምሪያ ምክትል ሃላፊነት ወደ ጎንደር ከተማ ከንቲባነት በአጭር ጊዜ ማደጋቸው የተገለጸው አቶ ተቀባ ተባባል፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወዲህ ለስርዓቱ በፍጹም ታማኝነት በማገልገል ላይ መሆናቸውም ተመልክቷል።
በዚሁም በርካታ ወጣቶች እንዲታሰሩና እንዲገደሉ በማድረጋቸው በአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚጠሉና እንደሚወቀሱ ለኢሳት የደረሰው ዜና ያሰረዳል።
የመብት ጥያቄያቸው የሃይል ምላሽ ሲሰጠው ሃብት ንብረታቸውን ጥለው ወደ በረሃ የወረዱት አቶ ጎቤ መልኬ በመገደላቸው እኚሁ ከንቲባ ለብሄራዊ መረጃና ደህንነት ባልደርቦችና ለመከላከያ ባለስልጣናት በሆቴል የደስታ ግብዣ በማድረጋቸው የተቆጩ ወገኖች ጥቃቱን ፈጽመዋል የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነው። ኢሳት ግን ስለድርጊቱ ፈጻሚዎችና ትክክለኛ አላማቸው ለማወቅ አልቻለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ጥቃቱ በተፈጸመ ማግስት ዕሁድ የካቲት 26 2009 በዚሁ በጎንደር ከተማ አውቶ ፓርክ በተባለው አካባቢ ያልታወቁ ታጣቂዎች በፌዴራል ፖሊስ አባላት ላይ ድንገተኛ ተኩስ ከፍተዋል።
ባልተጠበቀ ተኩስ የተደናገጡት የፌዴራል ፖሊስ አባላት ደባልቄ በተባለ ድልድድ አድርገው ወደ ቀበሌ 10 ሸሽተዋል በማለት ለኢሳት የገለጹት ምንጮች ታጣቂዎቹ ከአካባቢው መሰወራቸውንም አስረድተዋል።
የተኩስ ድምፅ በመሰማቱ በአካባቢው በተፈጠረው ድንጋጤ አንድ ፒክአፕ መኪናና ባጃጅ ተሽከርካሪዎች መጋጨታቸው ተመልክቷል። በመኪኖቹ ላይ ከደረሰው ግጭት ውጭ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።