በጎንደር ከተማ አንድ ሆቴል ውስጥ ጥቃት ተፈጽሞ በሰዎችና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

ኢሳት (መጋቢት 25 ፥ 2009)

በጎንደር ከተማ ፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል ላይ ቅዳሜ ምሽት የቦምብ ጥቃት ደረሰ። ጥቃቱ የተፈጸመበት ባለሶስት ኮከብ ሆቴል በአብዛኛው የወታደራዊ አዛዥ ጄኔራሎችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የሚያርፉበት እንደኾነ እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።

ማራኪ ተብሎ በሚታወቀው የጎንደር ዩኒቨርስቲ አካባቢ በሚገኘው በዚሁ ሆቴል የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ሶስት ሰዎች መቁሰላቸውን ለማወቅ ተችሏል። ለጥቃቱ እስካሁን ሃላፊነት የወሰደ አካል የለም።

በዚሁ በፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል የደረሰው ጥቃት በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ላይ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ በጥቃቱ ሶስት ሰዎች ቆስለው የሆቴሉ መስታዎቶችም መሰባበራቸው ታውቋል። እንደ አይን ምስክሮች ገለጻ በፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል የወታደራዊ ዕዙ (ኮማንድ ፖስት) ጄኔራሎችና የመንግስት ባለስልጣናት በአብዛኛው የሚያርፉበትና ትዕዛዝ የሚሰጡበት ስፍራ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። አካባቢው አደጋኛ ቀጠና ተብሎ በከፍተኛ ጥበቃ የነበረበት ስፍራ መሆኑም ተገልጿል።

በፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል ጎንደር ከተማ የተፈጸመው የቦንብ ጥቃት ተከትሎ በርካታ የአካባቢው ሰዎችና መንገደኞች መታሰራቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል።

በጎንደር ከተማ ፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል ለተፈጸመ የቦምብ ጥቃት እስካሁን ሃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም። ይህም ሆኖ ግን በህዝቡ ውስጥ በአገዛዙ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ በመኖሩ ምናልባትም ጥቃቱ የደረሰው በስርዓቱ ላይ ተቃውሞ ያላቸው አካላት ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምቶች አሉ።

በጎንደር ከተማ የሚገኘው የፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባለቤት አቶ አባቡ ሃሽም የሚባሉ ግለሰብ ናቸው። በሆቴሉም በርካታ መንግስታዊ ዝግጅቶች የሚካሄዱበት እንደሆነ ታውቋል።

መንግስት በመጪው ሚያዚያ ወር የከተሞችን ቀን በጎንደር ከተማ ለማክበር ቀን ቆርጦ ዝግጅት ላይ ባለበት ወቅት ጥቃቱ መፈጸሙ ታውቋል።