በጎንደር ከተማ ቃጠሎ ለማስነሳት የሞከረች አንድ ሴት መያዟ ተነገረ

ኢሳት ( መስከረም 12 ፥ 2009)

በጎንደር ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ ሃሙስ ቀበሌ 14ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የኢሳት ቃጠሎ ለማስነሳት ከትግራይ ክልል መምጣቷ የተነገረ አንዲት ሴት በነዋሪዎች ቁጥጥር ስር መዋሏ ተገለጸ።

ለጊዜው ስሟ ያልታወቀው ተጠርጣሪ በአካባቢው ነዋሪዎች ከተያዘች በኋላ ለጸጥታ ሃይሎች ተላልፋ የተሰጠች ሲሆን ተጠርጣሪዋ በተሽከርካሪ ታጅባ በጎንደር ከተማ ስትዘዋወር የሚያሳይ የቪዲዮ ማስረጃ ይፋ ተደርጓል።

በድርጊቱ ቁጣ የተሰማቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተጠርጣሪዋን ይዞ ይጓዝ ከነበረው ተሽከርካሪ ዙሪያ በመሰባሰብ ቁጣቸውን ሲያሰሙ ታይተዋል።

በከተማው ረቡዕ ዕለት ቅዳሜ ገበያ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በቅርቡ ደርሶ ከነበረው ቃጠሎ የተረፉ ሱቆችን ለማቃጠል ቤንዚን ይዘው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አራት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ምንጮች ለኢሳት መግለጻቸው ይታወሳል።

አራት ተጠርጣሪዎች ከትግራይ ክልል መምጣታቸውን የተናገሩት እማኞች ተጠርጣሪዎች ሊፈጽሙት የነበረው ጥቃት በጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ መቀስቀሱ ታውቋል።

በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙት ተጠርጣሪዎች ለፖሊስ በሰጡት ቃል እነሱን ጨምሮ ወደ 50 የሚጠጉ ሰዎች ለተመሳሳይ ድርጊት መሰማራታቸውን ማመናቸውን ከምንጮች ለመረዳት ተችሏል።

ሃሙስ በቁጥጥር ስር የዋለችውና በፖሊስ ምርመራ ላይ የምትገኘው ሴት አደጋው ለማድረስ ተሰማርተዋል ከተባሉት መካከል አምስተኛ ስትሆን፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ከቀናት በፊት በከተማዋ ቅዳሜ ገበያ ተብሎ በሚጠራ የገበያ መንደር በደረሰ የእሳት ቃጠሎ በርካታ ሱቆች መውደማቸው ይታወሳል።