በጎንደር እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ ለማስቆም ለተለያዩ ግብዓቶች ማስፈጸሚያ የ3.5 ሚሊዮን ብር በጀት ጥያቄ ቀረበ

ኢሳት (ነሃሴ 30 ፥ 2008)

በጎንደር ከተማና ዙሪያዋ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ እልባት አለማግኘቱን ተከትሎ የከተማው አስተዳደር የክልሉ መንግስት ለጸጥታ ሃይሎች ለሚውሉ የተለያዩ ግብዓቶች ማስፈጸሚያ የ3.5 ሚሊዮን ብር ልዩ የበጀት ጥያቄን አቀረበ።

የከተማዋ አስተዳደር እስከ ነሃሴ አምስት 2008 ዓም ድረስ ለጸጥታ ሃይሎች ምግብና የስልክ አገልግሎቶች እንዲሁም ለእስረኞች የምግብ አቅርቦት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን የክልሉ መንግስት ባቀረበው ባለ አራት ገጽ ሪፖርት አመልክቷል።

ይሁንና ታቃውሞ በአካባቢው ዘላቂ ይሆናል ተብሎ በመሰጋቱ ምክንያት የአማራ ክልል ብሄራዊ ምክር ቤት ችግሩን ተረድቶ የተጨማሪ የ3.5 ሚሊዮን ብር በጀት ድጋፍ እንዲያደርግ በከተማዋ ከንቲባ አቶ ጥላሁን መኳንንት ሰብሳቢነትና በ17 የአስተዳደሩ አባላት ተፈርሞ የቀረበው ደብዳቤ በዝርዝር አስፍሯል።

ይኸው ለኢሳት የደርሰውና የበጀት ጥያቄን የያዘው ባለሁለት ገጽ ደብዳቤ ህዝባዊ ታቃውሞ ቀጣይ እንደሚሆን ለክልሉ መንግስት አስረድቷል።

እስካሁን ድረስ የጎንደር ከተማ ወጭ አድርጊያለሁ ያለውን የአንድ ሚሊዮን 27ሺ ብር ወጪን ጨምሮ የክልሉ መንግስት በአጠቃላይ የአምስት ሚሊዮን ዘጠና አራት ሺ ሰባ ስድስት ብር የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ እንደቀረበበት ለመረዳት ተችሏል።

ለጸጥታ ሃይሎች የምግብና የሞባይል ስልክ ወጪዎችን የጎንደር ከተማ አስተዳደር በእስካሁኑ ቆይታው ከ400 ሺ ብር በላይ ውጪን አድርጊያለሁ ብሎ የገለጸ ሲሆን፣ ለእስረኞች ዳቦ አቅርቦት ዳግም 95 ሺ ብር መዋሉን በደብዳቤው አመልክቷል።

ይሁንና የከተማዋ አስተዳደር ከተቃውሞ ጋር በተገናኘ ምን ያህል ሰዎች ለእስር እንደተዳረጉ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።