በአዲስ አበባም የስራ ማቆም አድማ ተጠርቷል
ነሃሴ ፬ ( አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኮሎኔል ደመቀ ዘውዴን የፍርድ ቤት ቀጠሮ ለመከታተል በርካታ ህዝብ በፍርድ ቤቱ ዙሪያ ተገኝቶ ሲጠባበቅ የዋለ ቢሆንም፣ ኮሎኔሉ ፍርድ ቤት ባልቀረቡበት ሁኔታ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል። በድርጊቱ የተበሳጩት የከተማዋ ነዋሪዎች ተቃውሞአቸውን ገዢውን ፓርቲ በማውገዝ እና መንገዶችን በድንጋይ በመዝጋት የገለጹ ሲሆን፣ ከተማዋን የወረሩት ልዩ ኮማንዶ የሚባሉት፣ የአጋዚ ወታደሮችና የፌደራል ፖሊስ አባላት ወጣቶችን እንዲበተኑ አድርገዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችም ተይዘው መታሰራቸው ታውቋል።
ጎንደር እንደሰሞኑ ሁሉ አሁንም በውጥረት ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፣ ህዝቡን ለማረጋጋት የሚጥሩት የብአዴን ከፍተኛ ባለስልጣናት በወጣቶች ክፉኛ ተተችተው እቅዳቸውን ሳያሳኩ ቀርተዋል። አሁንም በተለያዩ የሰሜን ጎንደር ዞኖች የከተማውን ነዋሪና አርሶአደሮችን ለማሳመን የሃይማኖት አባቶች ደፋ ቀና እያሉ ሲሆን፣ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች በግልጽ የገዢው ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ናቸው በሚል ነቀፋ እየተሰነዘረባቸው ነው።
በአቡነ ማትያስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ሆነ የእስልምና ጉዳዮች ኮሚቴ ወታደሮች ከ160 በላይ ዜጎችን በአንድ ሳምንት ውስጥ ሲገደሉ ድርጊቱን አለማውገዛቸው የአካባቢውን ነዋሪዎች አሳዝኗል።
በባህርዳር አሁንም ውጥረቱ እንዳለ ሲሆን፣ ወታደሮች ወጣቶችን ከቤታቸው እየለቀሙ በማሰር ላይ ናቸው።
በሌላ በኩል ቅዳሜ ነሐሴ 7 ቀን በምእራብና መስራቅ ጎጃም በዳንግላ፣ ኮሶበር፣ ቡሬ፣ፍኖተ ሰላም፣ደብረማርቆስ፣ሞጣ፣ብቸኛ ደጀን፣ደብረወርቅና ጉንደወይን እንዲሁም በሰሜንና ደቡብ ወሎ በ ደሴ፣ኮምቦልቻ፣ ከሚሴ፣ሸዋሮቢት፣ሀይቅ፣ ወልዲያ፣ አላማጣና ኮረም፣ መቄት፣ላስታ ላሊበላ፣ሰቆጣ፣ ራያ፣ ዋድላና ደላንታ የተቃውሞ ሰልፎችን ለማካሄድ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።
የየከተሞቹ ሕዝብ እንቅስቃሴ ያሰጋው መንግስትም የተቃውሞ ሰልፎቹ እንዳይካሄድ ለማደናቀፍ ከወዲሁ ታጣቂዎችን በማሰማራት ወጣቶችን ማፈስ እንደጀመረ ከየከተሞቹ የደረሱን ሪፖርቶች ያሳያሉ። ትናንት ማክሰኞ በሀይቅ ከተማ “ ወልቃይት አማራ ነው” የሚለውን የሻምበል በላይነህን ሙዚቃ ሲያዳምጥ የነበረ ወጣት በመንግስት ላይ ህዝብን እያነሳሳህ ነው ተብሎ በታጣቂዎች ተወስዷል። እነዲሁም ከዩኒቨርስቲ ለእረፍት የተመለሱ የኮረም ተማሪዎች “ተሰብስባችሁ መወያየት አትችሉም፡፡” ተብለው ከትግራይ ክልል በመጡ ፖሊሶች እየተዋከቡ መሆናቸው ተመልክቷል።
በወልድያ የቀበሊ ሊቀመንበሮች በየቀበሌው እየዞሩ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲመክሩ እያስጠነቀቁ ነው። በከተማዋ የሚካሄደው ፍተሻ እንደቀጠለ ሲሆን፣ ሃሙስ ከጥዎቱ 2:00ሰአት ላይ ደግሞ በወልድያ የባህል አዳራሽ የባጃጅ ባለንብርቶች እና ሹፌሮች አስቸኳይ ስብስባ ተጠርተዋል።
የፌደራል ፖሊሶች በየአደባባዩ በተጠንቀቅ ቆመው የሚታዩ ሲሆን የፌደራል ፖሊስ አምቡላንሶችም በከተማው በአቅጣጫው ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ።
በሱሉልታ ደግሞ አሁንም ወጣቶችን የማሰር ዘመቻው ተጠናክሮ ቀጥሎአል። ከ400 እስከ 500 የሚደረሱ ወጣቶች በእስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል።