በጎንደር አንድ የአርበኞች ግንቦት 7 አባል በ6 ፖሊሶች ላይ ጥቃት ፈጽሞ ራሱን አጠፋ

ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም አመሻሽ ላይ አምሳሉ ተሾመ የተባለው ታጋይ ሰዎችን በመመልመል ወደ በረሃ ተልካለህ ተብሎ በመጠርጠሩ፣ ፖሊሶች ሊይዙት ሲሞክሩ፣ እጄን አልሰጥም በማለት በያዘው ሽጉጥ አንድ የመቶ እልቅና ያለው መኮንንና ሌላ አንድ ተራ ፖሊስን በመግደል፣ እንዲሁም 4 ታጣቂዎች በማቁሰል በመጨረሻም በያዘው ሽጉጥ ራሱን አጥፍቷል።
ወጣቱ ከዚህ ቀደም የአርበኞች ግንቦት7 አባል ነህ በሚል ታስሮ የተፈታ ሲሆን፣ ባለፈው አርብ በድጋሜ ፖሊሶች ሊይዙት ሲመጡ ” አትቅረቡኝ ተመለሱ ” እያለ ማስጠንቀቁን ያልተቀበሉት ፖሊሶች ፣ እርምጃ ለመውሰድ ሲሞክሩ ታጋዩ ፈጥኖ እርምጃ በመውሰዱ በታጣቂዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ በራሱም ላይ እርምጃ መውሰዱን የአይን እማኞች ገልጸዋል።
ፖሊሶች በታጋዩ አስከሬን ላይ የማይገባ ድርጊት ለመፈጸም ሲሞክሩ ህዝቡ ” ከባህላችን የወጣ ነው” በማለት ተቃውሞ ማሰማቱንና ሟቹን ጀግና እያለ ሲያወድሰው መሰማቱን ፣ በህዝቡ ግፊትም አስከሬኑ ለቤተሰቡ ተሰጥቶ የቀብር ስነስርዓት መፈጸሙን ለመረጃው ቅርብ የሆኑ ሰዎች ለኢሳት ተናግረዋል።
ግንቦት7 ሬዲዮ በለቀቀው ዘገባ ደግሞ ታጋዩ 7 የኮልት ሽጉጥ ጥይቶችን ይዞ የነበረ ሲሆን፣ በ6ቱም ኢላማውን ከመታ በሁዋላ፣ የመጨረሻውን ጥይት በራሱ ላይ አውሎታል። ሬዲዮው የሟቾቹን ቁጥር 3 መሆኑን ገልጿል።
ሳጅን ወለላው ዋናይሁን የተባለው የመተማ ወረዳ ፖሊስ የአመራር አባል አንድ በወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ለማዋል ሲሞክር ከነተከታዮቹ መገደሉንም ሬዲዮው ዘግቧል።
በሌላ በኩል ደግሞ በትክል ድንጋይና በሳንጃ ወረዳዎች የመንግስት ታጣቂዎች በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ወከባ እየፈጸሙ ነው። መንግስትን በሃይል ለማውረድ የሚታገሉትን ሃይሎች ትረዳላችሁ በሚል በርካታ ነዋሪዎች ተይዘው ታስረዋል። አብዛኞቹ በመንግስት ታጣቂዎች እየተደበደቡ መሆኑም ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የአካባቢው ህዝብ ከስርኣቱ ጋር ሆድና ጀርባ በመሆኑ የተቃዋሚ ሃይሎችን እየረዳና እየደገፈ እንደሚገኝ፣ ይህም መንግስት በቀል እርምጃውን እንዲያጠናክር እንዳደረገው ስማችን አይገለጸብን ያሉ ነዋሪዎች ተናግረዋል።