መስከረም ፲፩ (አሥራ አንድ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአገዛዙ ወታደሮች በጉልበት የንግድ ድርጅቶች እንዲከፈቱ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ውለዋል።
በአዲስ ዘመን የተሰማሩት የአጋዚ ወታደሮች ሱቆቻቸውን የማይከፍቱትን አስረዋል። በባህርዳር ደግሞ በርካታ ነጋዴዎች ከታሰሩ በሁዋላ ለቤተሰቦቻቸው ስልክ እየደወሉ ሱቆቻቸውን እንዲከፍቱ ለማስገደድ ተሞክሯል።
በጎንደር ህዝቡ ከስራ ማቆም አድማው ጋር በተያያዘ ለተቸገሩት ነዋሪዎች ምግብ በጋራ ሆኖ እያቀረበ ነው።
በከተሞች ታሪክ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ታሪክ ረጅም ሊባል የሚችል የስራ ማቆም አድማ በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማና በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳር እንዲሁም ህዝባዊ ትግሉ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ አገዛዙን በከፍተኛ ደረጃ እየተቃወች በምትገኘው አዲስ ዘመን ከተማ ተጠናክሮ ቀጥሎአል።
የንግድ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ በመዘጋታቸው እንዲሁም በመንገድ ላይ የሚታየው እንቅስቃሴ በእጅጉ በመቀነሱ ጎንደር ከተማ አስፈሪ ድባብ ይታይባታል። የአጋዚ ወታደሮች ደፍረው በነጋዴዎች ላይ እርምጃ ባይወስዱም፣ አሁንም በከተማው ላይ እየተመላለሱ የስነ ልቦና ጫና ይፈጥራሉ። የከተማው ወጣቶች ራሳቸውን በማደራጀት በስራ ማቆም አድማው የተነሳ ለተቸገሩ ሰዎች ምግብ አቅርበዋል።
በባህርዳር ደግሞ ነጋዴዎች ለአንድ ቀን ከታሰሩ በሁዋላ የንግድ ድርጅቶቻቸውን እንፍታለን ብላችሁ ቃላችሁን ስጡ እየተባሉ ከእስር ተለቀዋል። ይሁን እንጅ አልፎ አልፎ በቀበሌ 11 አካባቢ አንዳንድ ሱቆች ከመከፈታቸው ውጭ በዋና ዋና ቦታዎች ላይ የንግድ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ እንደተዘጉ ናቸው። የብአዴን ዋና ጸሃፊና ም/ል ጠ/ሚኒስትሩ ከከተማው ከንቲባ ጋር በመሆን ነጋዴዎችን ለማስፈራራት ሙካ አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ ነጋዴው ግን ለማስፈራሪያው አልተንበረከከም።
በአዲስ ዘመንም እንዲሁ የአጋዚ ወታደሮች በብዛት ተሰማርተው ነጋዴዎችን ከፍቱ እያሉ፣ አንከፍትም ያሉትን እየወሰዱ አስረዋል።
በንፋስ መውጫ ዛሬ የስራ ማቆም አድማ መጀመሩንም ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።