ኢሳት ((ሃምሌ 12 ፥ 2008)
ረቡዕ ዕለት በጎንደር ከተማ ይካሄዳል የተባለውን የእግር ኳስ ጨዋታ ተከትሎ ተጨማሪ መከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ ጎንደር ከተማ መግባታቸው ታወቀ።
የአማራ ክልል የአካባቢ ሚሊሺያዎች መሳሪያቸውን ይዘው በቤታቸው እንዲወሰኑም መመሪያ መውረዱን ከጎንደር ለኢሳት የደረሰው ዜና ያስረዳል።
ረቡዕ ሃምሌ 13 ፥ 2008 ዓም በጎንደር ስታዲያም በኢትዮጵያ መድህን ድርጅትና በፋሲል ከነማ መካከል ሊካሄድ መርሃ ግብር የተያዘለት ፕሮግራም ህዝባዊ ቁጣ ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት ደቅኗል። በዚህም ሳቢያ የመከላከያ ሰራዊት በከፍተኛ ቁጥር እንዲገባ መደረጉንም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መርሃ ግብሩ እንዲሰረዝ፣ ወይንም ወደ ሌላ ስፍራ እንዲዛወር በአንዳንዶች ዘንድ ግፊቶች ቢታዩም በስልጣን ላይ ያሉት ወገኖች አካባቢው ተረጋግቷል ካሉ በኋላ ጨዋታውን መሰረዝ ወይንም ማዛወር የፖለቲካ ጉዳት ይኖረዋል በሚል ጨዋታው እንዲደረግ መወሰናቸውን መረዳት ተችሏል።
ሆኖም የአማራ ክልል ሚሊሺያዎች ትጥቅ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ተቃውሞን ተቀላቅለው ጉዳት ያደርሳሉ የሚል ስጋት በመፈጠሩ በቤታቸው እንዲወሰኑ መመሪያ ደርሷቸዋል። ረቡዕ 9 ሰዓት በጎንደር ስታዲየም በመድህን ድርጅትና በፋሲል ከተማ መካከል የሚካሄደውን ውድድር በተመለከተ ሙሉ በሙሉ ጸጥታውን የመከላከያ ሰራዊት እንዲያስከብርም ዝግጅት መጠናቀቁ ታውቋል።
ባለፈው ሳምንት በባህር ዳር ከነማና በመቀሌ ከነማ መካከል በባህር ዳር ሊካሄድ የነበረው የእግር ኳስ ጨዋታ ወደ አዲስ አበባ መዛወሩን መዘገባችን ይታወሳል። ጨዋታው ወደ አዲስ አበባ ከመዛወሩ በፊት አዳማ ላይ እንዲካሄድ ተወስኖ የነበረ ሲሆን፣ እዚያም ረብሻ ይነሳል በሚል ወደ አዲስ አበባ መዛወሩ ታውቋል።