ታኅሣሥ ፯ (ሰባት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የውጥረቱ መነሻ ከኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ጋር የተያያዘ ነው። ቀደም ብሎ ኮ/ል ደመቀን አጅበው ወደ ፍርድ ቤት የሚወስዱ ሃይሎች ተለውጠው አዳዲስ ሃይሎች ኮሎኔሉን አጅበን እንወስዳለን ማለታቸውን ተከትሎ ኮ/ል ደመቀ ፣ “ አልሄድም ፣ አሞኛል”፣ የሚል መልስ በመስጠታቸው ውዝግብ መነሳቱ ታውቋል። አዲሶቹ የእስር ቤቱ ሃላፊዎች “ እኛን ታስጠይቀናለህ፣ መሄድ አለብህ” ብለው ልመና የገቡ ቢሆንም፣ ሌሎች እስረኞች በአንድነት በመውጣት ከታጣቂዎች ጋር በመፋጠጣቸው ኮሎኔሉ ሳይሄዱ ቀርተዋል።
ፍርድ ቤቱም ኮሎኔሉ በሌሉበት ለጥር 15 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል። የእስር ቤቱ ሃላፊ የነበሩት ኢንስፔክተር ልጃለም መሰረት፣ ኮሎኔሉን ያለካቴና ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አድርገዋል በሚል የታሰሩ ሲሆን፣ ጉዳያቸውን የሚያይላቸው ሰው በመጥፋቱ አሁንም ድረስ በእስር ላይ ይገኛሉ። እሳቸውን ለመተካት የተሾሙት ግለሰብ በሳምንት ውስጥ ሃላፊነቱን አልፈልግም ብለው ስልጣናቸውን አስረክበዋል። አዲስ የተሾሙት የዳባት ወረዳ የማረሚያ ቤት አዛዥ የነበሩት ናቸው።
የእስር ቤት ሃላፊዎችና ጠባቂዎች መለዋወጣቸው ኮ/ል ደመቀን ከጎንደር አውጥቶ ወደ አዲስ አበባ ወይም መቀሌ ለመውሰድ ያለውን ፍላጎት እንደሚያሳይ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ።