በጎንደር መድሀኒዓለም ቤ/ክ የተጠለሉ 48 ባህታዊያንን ወደ መጡበት ዋልድባ መወሰዳቸው ታወቀ

የካቲት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ባህታዊያኑ ከጥር 2 ቀን 2005 ዓም ጀምሮ በጎንደር ከተማ በሚገኝ መድሀኒአለም ቤ/ክርስቲያን ውስጥ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገላቸው ተጠልለው ቆይተዋል።

ትናንት ባህታዊያኑ ከቀኑ ስምንት ሰአት ላይ በአውቶቡስ ተጭነው ወደ አልታወቀ ስፍራ መወሰዳቸውን የዘገብን ሲሆን፣ ወኪላችን ሂደቱን ተከታትሎ እንደዘገበው ባህታዊያኑ የተወሰዱት ፣ ከተለያዩ የአማራ ክልል የተውጣጡ የሀይማኖት አባቶች ችግሩን በሽምግልና እንፈታዋለን የሚል ሀሳብ ካቀረቡ በሁዋላ ነው።

ባህታዊያኑ በአውቶቡስ ሲጫኑ የተመለከተ አንድ የጎንደር ነዋሪ ፣ እንደገለጠው ባህታዊያኑ ከህዝቡ እንዳይቀላቀሉ ሌት ተቀን ሲጠበቁ ሰንብተዋል (10፡42-11፡45 )

31ባህታዊያን ጥር 15 ቀን 2005 ዓም ለሰሜን ጎንደር ዞን መስተዳድር  እና ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን  በጻፉት አቤቱታ፣ ደረሰብን ያሉዋቸውን በርካታ በደሎች ዘርዝረው አቅርበዋል።

በደብዳቤው ፣ የጸለምት ወረዳ አስተዳደርን የተቆጣጠሩ ግለሰቦች ለዘመናት አንድነቱ ተከብሮና የዘር መድልዖ ሳይደረግበት ማንኛውም መናኝ በሀይማኖታዊ ምክንያቶች ብቻ ተመርምሮ ይኖርበት በነበረው ቦታ ግልጽ በሆነ መልኩ የትግራይ ክልል ተወላጅ ካልሆናችሁ በዚህ ገዳም መኖር አትችሉም በማለት ማህበረ-መነኮሳቱን መከፋፈላቸውን እንዲሁም  የአካካቢውን የሚሊሺያ ሀይል በመጠቀም የመብት ጥሰት መፈጸማቸው ፣ ተመልክቷል።

ከተጠቀሱት የመብት ጥሰቶች መካከል የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ መረሳ ማህበረ-መነኮሳቱን በዘር በመከፋፈልና የራሳቸውን የፖሊስ ታጣቂና ሚልሻ በመጠቀም እያሰሩ በተደጋጋሚ ማስደብደባቸው ተጠቅሷል።

ጥር 2 ቀን 2005 ዓም አባ ወ/ገብርኤል ገ/ስላሴ እና አባ ገ/ህይወት ተ/ማርያም የተባሉ መናንያን ከከዳሙ ተወስደው ሽፍታ መነኩሴዎች ተብለው ለ4 ቀናት መታሳራቸውን፣ የወረዳው አስተዳዳሪውም ” እናንተ ተመልሳችሁ ወደ ገዳሙ መግባት አትችሉም፣ የወጡትም አይመለሱም፣ በገዳሙ የቀሩትንም እየመነጠርን እናወጣቸዋለን፣ እንገባለን ካላችሁ ገዳያችሁን ሳታውቁ ትገደላላችሁ መባላቸውም ተመልክቷል።

” ከገዳሙ ለመውጣትም ሆነ ወደ ገዳሙ ለመግባት በምንቀሳቀስበት ጊዜም የትግራይ ክልል ነዋሪ መሆናችሁን የሚያሳይ የቀበሌ መታወቂያ ካላመጣችሁ እያሉ ያስገድዱናል የሚሉት ባህታዊያኑ ፣  የገዳሙን አስተዳደር ከወረዳ አስተዳደር የተላኩ ሚሊሺያዎችን ይዘው መምህር፣ እቃቤትና ሌሎች ሰራተኞችን በአዲስ አዋቅረዋል” ብለዋል።

የ31 መነኮሳትን ስም እና ፊርማ  የያዘው ደብዳቤ በተለያዩ ቀናት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በዝርዝር ከመያዙም በላይ፣  ፖለቲካን ተገን ያደረገው ዘረኛ  አስተሳሰብ በገዳሙ የመቀጠል መብታቸውንና የማህበረ መነኮሳቱን ህልውና  አደጋ ላይ መጣሉን አመልክቷል።

መነኮሳቱ ያቀረቡትን አቤቱታ በተመለከተ የጸለምት ወረዳ ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።