በጎንደር መስተዳድሩ ተቃውሞ ባሰሙ ድርጅቶች ላይ ቅጣት እየጣለና ድርጅቶች እንዳይከፈቱ እያገደ ነው

መስከረም ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በአማራ ክልል በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ ትግል ተከትሎ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ለሳምንታት ያካሂዱት የስራ ማቆም አድማ ያበሳጫቸው የክልሉ ባለስልጣናት፣ የንግድ ድርጅቶች እየመረጡ በመክፈትና እየመረጡ ቅጣት በመጣል ፣ ህዝቡን ለመከፋፈል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነዋሪዎችን አበሳጭቷል።

አንዳንድ የባጃጅ አሽከርካሪዎች 500 ብር እና ለሁለት ሳምንታት ያክል ስራ እንዳይሰሩ የታገዱ ሲሆን፣ አንዳንድ ሆቴሎች ደግሞ እንዳይፍቱ እገዳ ተጥሎባቸዋል። ነጋዴዎቹ ለምን ብለው ሲጠይቁ እናንተ ሌሎች ሲያዘጉዋቸው ከዘጋችሁ፣ እኛም ዝጉ ስንል የመዝጋት ግዴታ አለባችሁ የሚል መለስ እንደሚሰጣቸው ነጋዴዎች ተናግረዋል።

ሁኔታው ያበሳጫቸው የከተማዋ ነዋሪዎች አገዛዙ ሆን ብሎ ህዝቡን በመከፋፈል ትግሉን ለማዳከም የወጠነው እቅድ በመሆኑ ህዝቡ እስካሁን እንዳሳየው ሁሉ አሁንም በአንድነት ሆኖ ሊታገል እንደሚገባ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ስርዓቱ ያገዳቸው የንግድ ድርጅቶች ስራ እንዲጀምሩ እንዲሁም በባጃጅ አሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው የገንዘብ ቅጣት እንዲቀርና እገዳውም እንዲነሳ ለማስገደድ የአድማ የጥሪ ወረቀቶች  ሲበተኑ መዋላቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።