በጎንደርና ባህርዳር የስራ ማቆም አድማው ለሁለተኛ ቀን ቀጥሏል

በጎንደርና ባህርዳር የስራ ማቆም አድማው ለሁለተኛ ቀን ቀጥሏል
(ኢሳት ዜና የካቲት 13 ቀን 2010 ዓ/ም) በአማራ ክልል የተጠራው የስራ ማቆም አድማ በጎንደር ከተማ ለሁለተኛ ቀን በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሎአል። በከተማው ምንም አይነት የንግድ እንቅስቃሴውም ሆነ የተሽከርካሪ አገልገሎት የለም። የአገዛዙ ካድሬዎች የንግድ ድርጅቶችን ለማስከፈት ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክልታል።
በባህርዳር ትናንት የተጀመረውን አድማ ተከትሎ የአገዛዙ ባለስልጣናትና ሰራተኞች የንግድ ድርጅት ባለቤቶችን እየደወሉና ወደ መስሪያ ቤታቸው እየጠሩ ሲያስፈራሩ ቢውሉም፣ በርካታ የንግድ ድርጅቶች ዛሬም አድማውን አድርገው ውለዋል። በዚህ የተበሳጩት ባለስልጣኑ በንግድ ድርጅቶች ላይ ታሽጓል የሚል ጽሁፍ ያለበት ወረቀት እየለጠፉ ነው።
ትናንት የአድማውን ጥሪ ባለመቀበል ሲሰራ የተገኘ ታክሲ ምሽት ላይ በከተማዋ ወጣቶች በፈንጅ ተመቷል። ዋናው ገበያ አካባቢ በሚገኘው ሚሊኒየም ካፌ አካባቢ ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ላይ በደረሰው ፍንዳታ የተጎዳ ሰው የለም። ጥቃቱን የፈጸሙት ሃይሎች ተቀጣጣይ ፈንጅ መጠቀማቸውን ከፖሊስ የተገኘው መረጃ የሚያመለክት ሲሆን፣ ፈንጁን ከመኪናዋ ጀርባ በማጥመድና ከመኪናዋ የኤሌትሪክ መስመር ጋር በማያያዝ፣ የመኪናው ሞተር እንደተነሳ ፍንዳታው እንደከሰት ማድረጉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡በመኪናዋ ወስጥ ከሾፌሩ ሌላ አንድ ሰው ብቻ የነበረ ሲሆን፣ በሰዎቹ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰም፡፡ ለጥቃቱ እስካሁን ሃላፊነቱን በይፋ የወሰደ አካል የለም።
አድማውን የሚያስተባብሩ ወጣቶች አድማውን በመጣስ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚሞክሩ ተሽከርከሪዎችን በንቃት እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸዋል።
በጎንደርና ባህርዳር የሚደረገው የስራ ማቆም አድማ የአስኳይ ጊዜ አዋጁ በታወጀ ማግስት የተደረገ መሆኑ፣ ህዝቡ አዋጁን ከምንም እንዳልቆጠረው የሚያሳይ ነው ተብሎአል።
የአድማው አላማ የታሰሩት እንዲፈቱ፣ አዋጁ እንዲነሳ እንዲሁም ህዝቡ ያነሳቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ የሚጠይቅ ነው።
በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የኢንተርኔት አገልግሎት ከተቋረጠ ረጅም ጊዜ በመሆኑ፣ አስተባባሪዎች በሁሉም አካባቢዎች አድማ ለመጥራት እንደቸገራቸው ይገልጻሉ። ያም ሆኖ በአጭር ጊዜ በተደረገ የመልክት ልውውጥ የተሳካ አድማ ማድረግ መቻሉ ህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄዎቹ ካልተመለሱለት ትግሉን ወደ ፊት ከመግፋት ወደ ሁዋላ እንደማይመለስ የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ አስተባባሪዎች ተናግረዋል።