በጎንደርና ባህርዳር አድማቸውን የጨረሱ ነዋሪዎች ወደ ስራ ቢመለሱም አንዳንድ የንግድ ድርጅቶች እየታሸጉ ነው

መስከረም ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ለ6 ቀናት በተከታታይ የተደረገው የጎንደር እና የባህርዳር ከተሞች የስራ ማቆም አድማ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ፣ ህዝቡ ከትናንት ጀምሮ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው ገብቷል። የተቃውሞው አስተባባሪዎች ህዝቡ ባሳየው ጽናትና ጀግንነት ኮርተናል ብለዋል። ከባድ ፈተና ቢሆንም፣ ፈተናው በድል ተወጥተናል በቀጣይም ሌሎች የትግል ስልቶችን ተግባራዊ እናድርጋለን በማለት ተናግረዋል። የሁለቱም ከተሞች ህዝብ በአንድነት በመናበብ ያካሄደውን የስራ ማቆም አድማ ታሪካዊ ሲሉ ያኮላሹት አስተባባሪዎች፣ ገዢው ፓርቲ አሁንም ለህዝብ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑ ትግሉን አጠናክረን እንድንገፋበት ያደርገናል ብለዋል።

በጎንደር ዛሬ በርካታ ሆቴሎች እና የንግድ ድርጅቶች በአድማው ተሳትፈዋል በሚል ተዘግተዋል። በባህርዳር አንዳንድ ሱቆች ድርጅቶቻቸውን እንዳይከፍቱ አሁንም እገዳ እንደተጣለባቸው ነው።

በሰሜን ጎንደር  በሁሉም ወረዳዎች ከህዝባዊ ተቃውሞው ጋር በተያያዘ ህዝቡ የመስቀል በአልን በአደባባይ እንደማያከብር ስምምነት ላይ መደረሱን አስተባባሪ ኮሚቴው ገልጿል።

በአዲስ አበባ የደመራ በአል በከፍተኛ የጸጥታ ቁጥጥር የተካሄደ ሲሆን፣ የጸጥታ ቁጥጥሩ በበአሉ ድምቀት ላይ ከፍተኛ ጥላ አጥልቷል። በሌላ በኩል በሶማሊ ክልል በጅጅጋ ከተማ በአማራ እና ኦሮምያ የተካሂዱትን ህዝባዊ ተቃውሞች የሚያወግዝ ሰልፍ እየተዘጋጀ ነው።

ጅጅጋ: ለነገ ከጥዋቱ 12 ሠዓት ጀምሮ የግዳጅ ሠልፍ እንድንወጣ በክልሉ መንግሥት ታዝዋል .ከሠልፉ በሚቀር እርምጃ እንወሥዳለን እያሉ ነው. አሁን ከተመዋ በፌደራል ተወራለች እኔ በግል ት/ት ቤት የምሠራ መ/ር ነኝ የክልሉ ፕሬዘዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር ዛሬ መስከረም 16፣ 2009 ዓም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመሰብሰብ ማክሰኞ መስከረም 17 ፣ 2009 ዓም ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተነሱት ህዝባዊ ተቃውዎችሞ እንዲያወግዝ መመሪያ አስተላልፈዋል።

ፕሬዚዳንቱ በኦሮምያ በአማራ ክልሎች የሚካሄደው ተቃውሞ ህገ-መንግስቱን ለመናድ ያለመ  የትምክህተኞችን ና ጠባቦች ሴራ ነው ብለዋል። በሰልፉ ላይ ያልተገኙትን ሰራተኞ እንደሚያባርሩ፣ የአማራንና የኦሮሞ ተወላጅ ነጋዴዎችም ንግድ ፈቃዳቸውንና ንብረታቸውን እየተቀሙ ከክልሉ እንደሚባረሩ ፕሬዚዳንቱ ዝተዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በፌስቡክ ጽሁፎችን አውጥታችሁዋል በሚል ወጣቶች እየታደኑ  በጅጅጋ ፖሊስ መምሪያ እታሰሩ ነው። ፍጹም ምትኬ ና መኮነን የሚባሉ ወጣቶች ታስረው ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን የደረሰን መረጃ ያሳያል።