በጎረቤት ሀገር ሱዳን ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 30/2010)

በዳቦ ዋጋ ላይ የተደረገ ጭማሪ በጎረቤት ሀገር ሱዳን ከፍተኛ ተቃውሞ ቀሰቀሰ።

በአራት ከተሞች ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን የገለጸ ሲሆን በዚህም ተቃውሞ አንድ ሰው ሲገደል 6 ቆስለዋል።

አመጹን አስነስተዋል በሚል ሶስት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ሲታሰሩ 6 ጋዜጦች ተዘግተዋል።

በምዕራብ ዳርፉር ግዛት የተጀመረው ተቃውሞ ርዕሰ መዲናዋ ካርቱም መድረሱም ታውቋል።

አልጀዚራ እንደዘገበው ትላንት እሁድ በምዕራብ ዳርፉር ግዛት መዲና ጌኒና የተጀመረው ተቃውሞ በከተማዋ ለአንድ ሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሲሆን 6 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ታውቋል።

የሱዳን መንግስት ስንዴ ከውጭ ማስገባቱን በማቆሙና በዳቦ ላይ ይደርግ የነበረውን ድጎማ እንዲሚያነሳ ባለፈው ወር ማስታወቁን ተከትሎ በተከሰተው የዳቦ ዋጋ መጨመር ተቃውሞ ወደ ደቡብ ምዕራብ ሱዳን ኒያላና አልዴማዚን ከተሞች ተሸጋግሯል።

በዚህም ሳይወሰን የሀገሪቱ ርዕሰ መዲና የገባው ተቃውሞ በሀገሪቱ ከፍተኛ ውጥረት አስከትሏል።

የሱዳን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ለመንግስታዊው ዜና አገልግሎት ሱና በሰጡት መግለጫ የተቃውሞ ሰልፉ ከዳቦ ዋጋ ጋር የተያያዘ አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል።

ረብሻ በሚፈጥሩት ሃይሎች ላይ የሃይል ርምጃ እንደሚወስዱም አሳስበዋል።

የዳቦ ዋጋ በእጥፍ መጨመሩን ተከትሎ ከተቀሰቀሰው አመጽ ጋር በተያያዘ እስካሁን ይፋ በሆኑ መረጃዎች አንድ ሰው ሲገደል 6 ደግሞ መቁሰላቸው ታውቋል።

ሶስት የተቃዋሞ ፓርቲ መሪዎች ሲታሰሩ 6 ጋዜጦች ታግደዋል።

እንዲሁም በዳቦ ዋጋ ላይ ይደረግ የነበረው ድጎማ መነሳቱን የተቹ ጋዜጦችም ከታተሙ በኋላ ስርጭታቸው ታግዷል።

167 የሱዳን ፓውንድ ይሸጥ የነበረው 50 ኪሎ ስንዴ የሱዳን መንግስት ድጎማውን በማቋረጡ በሶስት እጥፍ በመጨመር 450 ፓውንድ ወይንም 25 የአሜሪካ ዶላር መግባቱ ለችግሩ መከሰትና ለቀውሱ መባባስ ምክንያት ሆኗል።

መንግስት በነዳጅ ላይ ያደርግ የነበረውን ድጎማ ማንሳቱን ተከትሎ እንደ አውሮፓውያኑ በ2013 ተመሳሳይ ተቃውሞ መከሰቱም ተዘግቧል።