ኢሳት ዜና (ግንቦት 11 ፥ 2008)
ትናንት ማክሰኞች ሌሊት ከፓሪስ 66 ሰዎችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረ የግብጽ አየርመንገድ አውሮፕላን በሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ በመከስከሱ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት ሁሉም ተሳፋሪዎቹ መሞታቸው ተገለጸ።
ኤር ቡስ 320 የተባለው ይኸው አውሮፕላን ትናንት በመጀመሪያ 90 ዲግሪ ወደግራ፣ ቀጥሎ 360 ዲግሪ ወደቀኝ በመሽከርከር ከ7.5 ኪሎሜትር ከፍታ ተምዘግዝጎ በሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ መውደቁን የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በ2003 ዓም የተመረተውና ኤር ቡስ ኤ320 የተባለው ይኸው አውሮፕላን አቅጣጫውን ከሳተ በኋላ ወዲያውኑ ከራዳር ዕይታ ውጭ መሆኑን ተነግሯል። አውሮፕላኑ የወደቀበት ቦታ የግብጽ ባህር ዳርቻ ለመድረስ 174 ማይል ሲቀረው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
የግብጽ የሲቪል አየር መንገድ ሃላፊዎች እንደተናገሩት፣ አውሮፕላኑ በቴክኒካዊ ብልሽት ሳይሆን በአሸባሪዎች ጥቃት ደርሶበት ሳይወድቅ እንዳልቀረ ፍንጭ ሰጥተዋል።
በአውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩት 66 ተሳፋሪዎች መካከል 55ቱ መንገደኞች ሲሆኑ፣ 3 የግብፅ የጸጥታ ሰራተኞች ፣ ሰባት የአውሮፕላኑ ሰራተኞች እንደነበሩ ታውቋል።