በግብፅ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት 44 ሲሞቱ ከ 100 በላይ መቁሰላቸው ተገለጸ

ኢሳት (ሚያዚያ 2 ፥ 2009)

በግብፅ በሁለት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያኖች ላይ ዕሁድ በተፈጸመው የቦንብ ጥቃት የሟቾች ቁጥር 44 መድረሱንና ከ100 በላይ ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሃገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በቤተ-ክርስቲያኖቹ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በማውገዝ የግብፅ ፕሬዚደንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ጉዳዩን በአግባቡ እንደሚይዙት ገልጸዋል።

ከተለያዩ የአለም አቀፍ ሃገራትና ተቋማት እየቀረበ ያለውን ውግዘት ተከትሎ ግብፅ የሶስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ እንዲታወጅ ማድረጉን ሮይተርስ ዘግቧል።

የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን የቦንብ ጥቃት ታንታ ተብሎ በሚጠራ ከተማ ላይ የተፈጸመ ሲሆን፣ በዚሁ ጥቃት በትንሹ 27 ሰዎች ሲገደሉ 78 የሚሆኑ ደግሞ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተመልክቷል።

በቤተ-ክርስቲያኑ የጸሎት ክፍል ውስጥ በሚገኝ ወንበር ላይ የተቀመጠ ቦንብ አደጋው እንዲደርስ ምክንያት መሆኑን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተወካዮች ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል። በአሌክሳንድሪያ ከተማ በሚገኘው የቅዱስ ማርቆስ የኦሮቶዶክስ ካቴድራል ላይ በአንድ አጥፍቶ ጠፊ በተፈጸመው ጥቃት ደግሞ በትንሹ 17 ሰዎች ተገድለው 41 የሚሆኑት ምዕመናን ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የፋሲካ በዓል አንድ ሳምንት ሲቀረው የሚከበረውን ልዩ ሃይማኖታዊ ስነስርዓት ለመታደም በርካታ ሰዎች በቤተክርስቲያኖቹ ተገኘተው የነበረ ሲሆን፣ ጥቃቱም ሆን ተብሎ የተቀነባበረ መሆኑን የግብፅ ባለስልጣናት ይገልጻሉ።

በአሌክሳንድሪያ ከተማ በሚገኘው ቤተ-ክርስቲያን የኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ ቴዎድሮስ ለሃይማኖታዊ ስነስርዓቱ ተገኘተው የነበረ ቢሆንም፣ ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ታውቋል። ጥቃቱን ተከትሎ ለህዝባቸው የቴሌቪዥን ንግግር ያደረጉት የግብፅ ፕሬዚደንት አልሲሲ ድርጊቱን በፈጸሙ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጸዋል።

ግብፅ ካላት ከ90 ሚሊዮን በላይ ህዝብ መካከል ክርስቲያኖች 10 በመቶ አካባቢ የሚሆነውን የሚሸፍኑ ሲሆን፣ በተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው የተለያዩ አካላት አስታውቀዋል።

በተያዘው ወር በሃገሪቱ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የሚጠብቁት ፓፕ ፍራንሲስ ጥቃቱን አውግዘው ጉብኝታቸው በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት ተግባራዊ እንደሚሆን መግለጻቸውንም መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ራሱን እስላማዊ ግዛት (ISIS) ብሎ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን ለጥቃቱ ሃላፊነት ወስዷል።

የህክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ ሰዎች የደም ልገሳን የሚፈልጉ በመሆናቸው ነዋርዎች የደም ልገሳ እንዲያደርጉ ጥሪን አቅረበዋል።

በግብፅ ያሉ ክርስቲያኖች በተደጋጋሚ ጥቃት የሚደርስባቸው በመሆኑ የሃገሪቱ መንግስት ልዩ ጥበቃን ማድረግ እንዳለበት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አሳስበዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አይሲስ በሃገሪቱ የተለያዩ ወታደራዊ ተቋማት ላይ ጭምር ጥቃት መውሰድ መጀመሩ ሲገልፅ ቆይቷል።

ባለፈው ሳምንት የግብፁ ፕሬዚደንት አብደል ፈታህ አልሲሲ በዚሁ በአሜሪካ ከአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ሽብርተኝነትን መዋጋት በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ መምከራቸው አይዘነጋም።

ታጣቂ ሃይሉ በቅርቡ የተለያዩ ጥቃቶችን ለመፈጸም ሲዝት መሰንበቱን ቢቢሲ ዘግቧል።

ሃገሪቱ ያወጀችውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሽብር የሚጠረጠሩ ሰዎችን ለማዳን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እርምጃን እንደሚወስድ ቢገለጽም፣ ጉዳዩ ለፓርላማ ቀርቦ መጽደቅ እንዳለበት ለመረዳት ተችሏል።