በግብጽ የመገናኛ ብዙሀን ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ ታዘዘ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 22/2010)

በግብጽ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሀን ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ የሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ታወቀ።

የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ተቋም የሆነው ሲ ፒ ጄ ባወጣው ሪፖርት እንዳመልከተው ከሆነ ጠቅላይ አቃቢ ሕጉ ትዕዛዙን ያስተላለፉት ለሃገሪቱ የህግ አካላትን መሆኑም ታውቋል።

የሀገሪቱ ምርጫ አንድ ወር ብቻ በቀረበት በዚህ ወቅት የሀሰት ዜናን ያሰራጫሉ በሚል መገናኛ ብዙሃንን ለማፈን ያደረገው ተግባር እንዳሳሰበውም በሪፖርቱ አስፍሯል።

በግብጹ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ትእዛዝ የሀሰት ዜናን ያሰራጫሉ ባላቸው አካላት ላይ ከቁጥጥር ባለፈ ፣ የሀገሪቱ ህግ አስፈጻሚ አካላት ርምጃ እንዲወስዱም ያዛል።

የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪው ተቋም ሲ ፒ ጄ እንዳወጣው ሪፖርት ከሆነ የሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ በሀገሪቱ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሀን ላይ የህግ አካላት ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረጉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

የሀገሪቱን የፍትህ ስርኣት አደጋ ውስጥ መሆኑን ማሳያ ነው ያለው ሲ ፒ ጄ ይህ ትዕዛዝ ከተላለፈ አንስቶ የግብጽ ባለስልጣናት አህመድ ታሪቅ የተባለ አክቲቪስትን ማስራቸውንና ሰልማ አላ አዲን ለተባለ ሰውም የእስር ማዘዣ ማውጣታቸውን ለማውቅ ተችሏል።

የመካከለኛው ምስራቅና የሰሜን አፍሪካ የ ሲ ፒ ጄ አስተባባሪ የሆኑት ሸሪፍ መንሱር እንዳሉት ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ጠንካራ ተቃዋሚ በሌለበት በሚወዳደሩበት በዚህ ምርጫ የግብጽ መንግስት ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ የማካሄድ እቅድ ካለው ይህ ትእዛዝ አስፈላጊ አልነበረም ብለዋል።

ሁኔታው እንዳሳሰበው ለግብጽ መንግስት የገለጸው ሲ ፒ ጄ ከህግ አካላቱ ምንም አይነት ምላሽ አለማግኘቱን አስታውቋል።

ፕሬዝዳንት አልሲሲ ስልጣን ከያዙ አንስቶ በሀገሪቱ እያጋጠመ ያለው የፕሬስ ነጻነት አፈና መባባሱንና  ኢፕሪል 6 የወጣቶች ንቅናቄ አባላትም እየታደኑ በመታሰር ላይ መሆናቸውን ነው ከተለያዩ አካላት እየወጡ ያሉ መረጃዎች የሚያመለክቱት።

አሶሼየትድ ፕረስና ሮይተርስ ትላንት የታሰረው ጋዜጠኛን በተመልከተም በዘገባቸው ላይ አስፍረዋል።

እንደ እነሱ ዘገባ ከሆነም ጋዜጠኛው ለእስር የተዳረገው ‘’1095 ቀናት’’ የሚል በፕሬዝዳንት አልሲሲ የስራ ቆይታ ላይ የሚያጠነጥን ዘጋቢ ፊልም በመስራቱ ምክንያት ነው።

በሀገሪቱ ውስጥ ስላለው የሰዎች አፈናን በተመለከተ የዘገበው ደግሞ ቢቢሲ ነው።

ቢቢሲ ይህንን ሪፖርት በማስፈሩም ከግብጽ ባለስልጣናት ሪፖርቱን እንዲያስተካክልና ይቅርታም እንዲጠይቅ ትዕዛዝ ተላልፎለታል።

የዜና ምንጩ ሃላፊዎች ግን ምንም የሰሩት ስህተት እንደሌለና ይቅርታም እንደማይጠይቁ በግልጽ አስቀምጠዋል።

ከተለያዩ ምንጮች የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ በሃገሪቱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከታህሳስ 2017 ጀምሮ እስካሁን 20 የሚሆኑ ጋዜጠኞች በእስር ላይ ይገኛሉ።