በግል ድርጅቶች የተቀጠሩ ስራቸውን በገፍ እየለቀቁ ነው

ሰኔ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፕሮቪደንት ፈንድ ያላቸውን የግል ድርጅት ሠራተኞችን ገንዘብ በመውሰድ በጡረታ እንዲተዳደሩ ለማድረግ የተረቀቀው የግል ድርጅቶች ማህበራዊ ዋስትና አዋጅ ማሻሻያ በበርካታ ሰራተኞች
ዘንድ ተቃውሞ ማስከተሉን ተከትሎ በተለይ ፕሮፌሽናል ባለሙያዎች የግል ድርጅቶችን በገፍ እየለቀቁና ለመልቀቅ የመልቀቂያ ደብዳቤ እያቀረቡ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት እየተሰራበት ያለው አዋጅ ቁጥር 715/2003 ለማሻሻል በምርጫው ማግስት ለፓርላማው የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከሰኔ 16/2003 ዓ.ም በፊት ተቀጥረው ይሰሩ በነበሩበት ድርጅቶች ውስጥ የፕሮቪደንት ፈንድ የነበራቸው የግል
ድርጅት ሠራተኞችን በግል ድርጅት ጡረታ እንዲሸፈኑ እንደሚደረግ፣ ከእንግዲህም የፕሮቪደንት አሰራር እንደማይኖር ይደነግጋል፡፡ ቀደም ሲል የተጠራቀመው የሰራተኞቹ ገንዘብም ወደመንግስት እንደሚገባም ይጠቅሳል፡፡ አብዛኛዎቹ የፕሮቪደንት
ፈንድ ያላቸው ተቁዋማት ሰራተኞች በረቂቅ አዋጁ የተበሳጩ ሲሆን በከፍተኛ የኩባንያ አመራር ቦታ ያሉና ፕሮፌሽናል ባለሙያዎችና ሌሎችም አዋጁ ከመጽደቁ በፊት ሥራቸውን በፍጥነት እየለቀቁ ያጠራቀሙትን የፕሮቪደንት ፈንድ ከባንኮች
እያወጡ መሆኑን ዘጋቢያችን ምንጮች ዋቢ በማድረግ ገልጿል። በዚህም የሠራተኞቹ እርምጃ ይበልጥ እየተጎዱ ያሉት የግል ባንክና ኢንሹራንሶች፣ የተለያዩ ኮርፖሬት ኩባንያዎች ሰራተኞች ይገኙባቸዋል፡፡
አንዳንድ ኩባንያዎች የቀረበላቸው መልቀቂያ ስላስደነገጣቸው ሰራተኞች ስራቸውን ሳይለቁ በስምምነት የፕሮቪደንት ፈንዳቸውን እየለቀቁላቸው መሆኑም ታውቋል፡፡
አንድ በባንክ ውስጥ የሚሰራ ባለሙያ በሰጠው አስተያየት የፕሮቪደንት ፈንድ ከሰራተኛውና ከአሰሪው ተዋጥቶ በሰራተኛው ስም የሚቀመጥ የአደራ ገንዘብ ሲሆን፣ ሰራተኛው በጡረታ ብቻ ሳይሆን ከበድ ያለ ማህበራዊ ችግር ሲገጥመው
አሰሪውን በማስፈቀድ ወጪ አድርጎ ሲጠቀምበት እንደቆየ አስታውሷል፡፡ አሁን መንግስት ብድግ ብሎ ባረቀቀው ሕግ ወደሃላ በመሄድ ገንዘባችንን እወርሳለሁ ማለቱ አበሳጭቶናል ብሎአል፡፡ ስለዚህም ስራዬን ለቅቄ ገንዘቤን ከወሰድኩ በሁዋላ
ሌላ ስራ ብፈልግ የተሻለ ያዋጣኛል ሲል አክሏል።