ኢሳት (ኅዳር 19 ፥ 2009)
በጌዲዮ ዞን ለተፈጠረው ግጭትና ለደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ተጠያቂው የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ነው ሲል በውጭ የሚኖሩ የጌድዮ ተወላጆች ኮሚኒቲ አስታወቀ። በውጭ ሃገር የሚኖሩ የጌዲዮ ተወላጆች የሚያስተባረው ማህበር በሰዎች ላይ ለደረሰው ሞት እንዲሁም ለደረሰብ ንብረት ውድመት ሃዘኑን በመግለጽ በአካባቢው ከሚኖሩ የሌላ አካባቢ ተወላጆች ኢትዮጵያውያን ጋር የጌዲዮ ህዝብ ችግር የለበትም ሲልም አመልክቷል።
ከወር በፊት በጌዲዮ ዞን የተፈጠረውን ችግርና የተከተለውን ሁኔታ በመዘርዘር ባለ 6 ገጽ መግለጫ ያወጣው የጌዲዮ ማህበር፣ የይገባኛል ጥያቄ ሲነሳበት በቆየው ቦታ ላይ ውሳኔ የተሰጠበት ጊዜ ለችግሩ መከሰትና መቀጣጠል ምክንያት መሆኑን አመልክቷል።
በሃገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የፖለቲካ አለመረጋጋት ባለበት ወቅት በአወዛጋቢ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ማስተላለፉ ተገቢ እንዳልነበርና ሆን ተብሎ ግጭት ለመቀስቀስ ያለመ ስለመሆኑንም የማህበረሰቡ መግለጫ ይዘረዝራል።
“የጌዲዮ ህዝብ በዞኑ ነዋሪ ከሆነ የህብረተሰብ ክፍል (ጉራጌ፣ ስልጤ፣ አማራ፣ ወላይታ፣ ኦሮሞ ሲዳማ ወዘተ) ጋር ምንም አይነት ችግር የለበትም፣ በጌድዮ ዞን ለተፈጠረው ቀውስ አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው የኢህአዴግ/ህወሃት መንግስት በዋናነት ተጠያቄ ነው” ያለው የጌዲዮ የማህበረሰብ መግለጫ ሲቀጥልም “ ከኢህአዴግ/ህወሃት የጌዲዮን ህዝብ በሙስና፣ በፍትህ ዕጦት፣ በመልካም አስተዳደር ችግር፣ በአንድ ብሄር የበላይነት በተፈጠረ የፖለቲካ ኪሳራ ምክንያት በተጨባጭ ቁልቁል እየወረደ ለሚገኘው የፖለቲካ ድርጅት የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ መጠቀሚያነት የሚያደርገው ተግባር በአስቸኳይ ይቁም! ድርጊቱንም እናወግዛለን!” በማለት በአካባቢው ለተፈጠረው ችግር ስልጣን ላይ ያለውን ቡድን ተጠያቂ ያደረገው የጌዲዮ ማህበረሰብ በመግለጫ፣ ግጭቱን ተከትሎ የጌድይ ምሁራንና ሌሎች የህብረተሰቡ ተወላጆች በመንግስት ሃይሎች ሰለባ መሆናቸውን አመልክቷል።
በጌዶዮ ምሁራን፣ በመንግስት ሰራተኞች በመካከለኛና ከፍተኛ ባለሃብቶች እንዲሁም በወጣቶችና ተማሪዎች ላይ እየተወሰደ ያለው የጅምላ ግድያ እና እስራት እንዲቆም ጥሪ በማቅረብም ድርጊቱን አጥብቀን እንቃወማለን ሲል መግለጫውን ቋጭቷል።