(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 7/2010) በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጅ በጌዲዮ ብሔረሰብ ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል መቀጠሉ እንዳሳሰበው በሰሜን አሜሪካና አውሮፓ የጌዲዮ ማህበረሰብ ማህበር አስታወቀ።
ማህበሩ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ለሚመለከታቸው የሃገር ውስጥና የውጭ ተቋማት በጻፈው ደብዳቤ እንዳስታወቀው ባለፈው 10 ቀናት ብቻ ከ2 መቶ በላይ የጌዲዮ ማህበረሰብ አባላት ሲገደሉ ከ3መቶ ሺህ በላይ ደግሞ ከሚኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለዋል።
ማህበሩ ከ137 የሚበልጡና በግፍ የተገደሉ የጌዲዮ ማህበረሰብ አባላትን ስም ዝርዝርም ይፋ አድርጓል።
በደቡብ ክልልና በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጅ ዞን የሚኖሩ የጌዶ ማህበረሰብ አባላት ቁጥራቸው 1 ነጥብ 5 ሚሊየን እንደሚደርስ በ1999 በተካሄደው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ተረጋግጧል።
እነዚሁ የብሔረሰቡ አባላት በእርሻ ስራና በቡና አምራችነታቸው ይታወቃሉ።
በኢትዮጵያ ሀገራቸው ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በፍቅርና በመተሳሰብ የሚኖሩ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን ሕልውናቸው አደጋ ላይ መውደቁን በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ የጌዶ ማህበረሰብ ተወካዮች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል።
ማህበሩ ለሚመለከታቸው አካላት በግልባጭ ጭምር ባሳወቀው ደብዳቤ እንደገለጸው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ የሚኖሩ የጌዶ ማህበረሰብ አባላት የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈጸመባቸው ይገኛል።
በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ኦቻ አማካኝነት በቀረበው ሪፖርት መሰረት ከኦሮሚያ ምዕራብ ጉጂ ዞን ከ4 መቶ ሺህ በላይ የጌዶ ማህበረሰብ አባላት ተፈናቅለዋል።
በግፍ የተገደሉት ደግሞ የሰሞኑን ሳይጨምር 125 ናቸው።
በምዕራብ ጉጂ 5ሺ የጌዶ ተወላጆች ቤት ሲቃጠል በዚሁ ሳቢያ ኑሯቸው የተመሰቃቀለባቸው በርካታ ናቸው ተብሏል።
እናም በሰሜን አሜሪካና አውሮፓ የጌዶ ማህበረሰብ ማህበር ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በጻፈው ደብዳቤ የዘር ማጥፋቱ በመቀጠሉ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ድርጊቱ በአሰቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል።
የጌዶ ተወላጆች ቋንቋቸውን የመጠቀም ባህላቸውን የማክበርና እምነታቸውን የማራመድ መብት ማጣታቸ የሚወገዝ ተግባር መሆን አለበትም ብሏል።
እናም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ የኦሮሚያ ክልልና አለም አቀፉ ማህበረሰብ የዘር ማጥፋት ድርጊቱን በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ ጠይቋል።
በሰሜን አሜሪካና አውሮፓ የጌዶ ማህበረሰብ ተወካዮች የ137 በግፍ የተገደሉ ሰዎችን ስም ዝርዝርም ይፋ አድርገዋል።