በጋዜጠኛ ተወልደ በየነ ላይ በሼህ አላሙዲን በሚደገፈው ኤሳ ዋን የተከፈተው ክስ ውድቅ ሆነ

ኢሳት (ሚያዚያ 27 ፥ 2016)

በሼህ መሃመር አላሙዲን የገንዘብ ድጋፍ በሰሜን አሜሪካ የሚንቀሳቀሰው AESA One (ኤሳ ዋን) የተባለው ተቋም በኢሳት ጋዜጠኛ ላይ የከፈተው ክስ ውድቅ ሆነ። በኢሳት የመዝናኛ ክፍል ጋዜጠኛ በሆነው beተወልደ በየነ ላይ በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት የተመሰረተው ክስ ውድቅ የተደረገው፣ ራሱ ከሳሽ አካል ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉና ክሱን በማቋረጡ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።

አመታዊ የስፖርት ውድድሮችን ለማካሄድ ባለፉት 4 አመታት በአንዳንድ የአሜሪካ ግዛቶች ሲንቀሳቀስ የቆየው ኤሳ ዋን፣ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶችንም ለማካሄድ በየአመቱ ከሃገር ቤት የሙዚቃ ባለሙያዎችን ሲጋብዝ ቆይቷል። በዚህ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ የኪነጥበብ ባለሙያዎች እንዳይገኙ በማስፈራራት በተቋሙ ላይ ኪሳራ አድርሷል በሚል በጋዜጠኛ ተወልደ በየነ ላይ የተመሰረተው ክስ ውድቅ መሆኑ የታወቀው በዛሬው ዕለት በዋለው ችሎት መሆኑን መረዳት ተችሏል።

ይህ በቢሊዮነሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሼህ መሃመድ አላሙዲን የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው ተቋም፣ ከ30 ዓመታት በላይ በሰሜን አሜሪካ የሚንቀሳቀሰውን የስፖርት ፌዴሬሽንን ለመሰንጠቅ ሞክሮ፣ በፍ/ቤት ስሙን እንዳይጠቀም ዕገዳ ከተጣለበት በኋላ ኤሳ ዋን በሚል አዲስ ስያሜ ሲጠራ አራት አመታት አስቆጥሯል።

ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ የስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ ለሁለት ለመክፈል የተደረገው ሙከራ መክሸፉን ተከትሎ ተቋሙ በኤሳ ዋን የጀመረው አመታዊ ውድድር የኢትዮጵያውያንን ትኩረት ባለመሳቡ፣ ይልቁንም ዋናውን የስፖርት ፌዴሬሽን ለማዳከም የተደረገ እንቅስቃሴ ነው በሚል ስነ-ስርዓቱ በተመልካች ድርቅ ሲመታ መቆየቱን መረዳት ተችሏል፥ ተቃውሞዎችም ሲቀርብበት ቆይቷል።

የኬነጥበብ ባለሙያዎቹ በዝግጅቱ እንዳይሳተፉ የሚያግባባውም እንዲሁም የሚያስፈራራው ጋዜጠኛ ተወልደ በየነ ነው በሚል ክሱ መመስረቱንም መረዳት ተችሏል።

ሆኖም ረቡዕ ዕለት ይኸው ክስ ውድቅ መደረጉም ተረጋግጧል። የቀድሞ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር አቶ ሬድዋን ሁሴን በአሜሪካ የገጠማቸው ተቃውሞ በማስመልከት በአክቲቪስት መኮንን ጌታቸው ላይ የመሰረቱት ክስ በተመሳሳይ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል።

በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በዋናነት ያቀፈውና፣ ከተለያዩ የአለም ክፍሎች የመጡ ኢትዮጵያውያን የሚታደሙበት ዓመታዊ የኢትዮጵያ የስፖርት ፌዴሬሽን፣ በሰሜን አሜሪካ ዝግጅት በመጪው ሰኔ ወር መጨረሻ በካናዳ ቶሮንቶ እንደሚካሄድም ለማወቅ ተችሏል። ኢትዮጵያውያን በቋንቋና በፖለቲካ አመለካከት ሳይለያዩ የሚታደሙበት ይህ ዝግጅት መከበር ከጀመረ ከ30 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። እኤአ ከፊታችን ጁላይ 3 እስከ 9 በካናዳ ቶሮንቶ ለ33ኛ ጊዜ ይከበራል።