በጋና ለ10 አመት ያህል አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሃሰተኛ የአሜሪካ ኤምባሲ መዘጋቱን አሜሪካ ገለጸች

ኢሳት (ኅዳር 26 ፥ 2009)

በጋና ለ10 አመት ያህል አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሃሰተኛ የአሜሪካ ኤምባሲ መዘጋቱን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ አደረገ።

በጋና መዲና አክራ ከአመታት በኋላ የተገኘው ይኸው ሃሰተኛ ኤምባሲ ለበርካታ ሰዎች በህገወጥ መንገድ የተገኙ ህጋዊ ቢዛዎችን እና የተለያዩ ሰነዶችን ሲሸጥ መቆየቱን የአሜሪካ ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ሃሰተኛ ኤምባሲ የአሜሪካ ሰንደቅ አላማን እንዲሁም የፕሬዜደንት ባራክ ኦባማ ምስልን በህንጻው ላይ ሰቅሎ ስራውን ያከናውን እንደነበር CNN ዘግቧል። amembassy-accra

ከአስር አመት በኋላ የተደረሰበት ሃሰተኛው የአሜሪካ ኤምባሲ በጋና እና በቱርክ የተደራጁ የወንጀለኞች ቡድን ይመራ እንደነበር የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክቷል።

በኤምባሲው ላይ በተካሄደው ወረራ የ10 ሃገራት 150 ፓስፓርቶች እንዲሁም የአሜሪካ፣ ህንድ፣ የደቡብ አፍሪካና የአውሮፓ መግቢያ ቢዛ ሊያዙ መቻሉን የቴለቪዥን ጣቢያው በዘገባው አቅርቧል። ለአገልግሎቱ ስድስት ሺ የአሜሪካ ዶላር ያስከፍል ነበር የተባለው ሃሰተኛ ኤምባሲ በ10 አመታት ውስጥ ምን ያህል ደንበኞችን እንዳስተናገደ እስካሁን ደረሰ የታወቀ ነገር የለም።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዚሁ ሃሰተኛ ኤምባሲ ቪዛን የተቀበሉ ሰዎች ወደ አሜሪካ ስለመግባታቸው ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን፣ ከዋናው ኤምባሲ ቪዛን ማግኘት ያልቻሉ ደንበኞች ወደ ሃሰተኛው ኤምባሲ በደላሎች ምክንያት ይሄዱ እንደነበር ታውቋል።

በጎረቤት ሃገራት ጭምር አገልግሎታቸውን ያስተዋወቁ ነበር የተባሉ ወንጀለኞች ምን ያህል እንደሆነ የተገለጸ ነገር ባይኖርም በሳምንት ሶስት ቀን ብቻ ክፍት የነበረው ሃሰተኛ ኤምባሲ በ10 አመታት ውስጥ በርካታ ሰዎችን እንዳስተናገደ ተነግሯል።

በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡ የጋና ባለስልጣናት በበኩላቸው ድርጊቱ መጠነ ሰፊ የሆነ ምርመራ እየተካሄደበት እንደሚገኝ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሃስተኛ ኤምባሲውን ሲመሩ የነበሩ አካላትን ከባለስልጣናት ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው መሆኑን አክሎ አስታውቋል።

በጋና ተመሳሳይ የኔዘርላንድ ሃስተኛ ኤምባሲ መገኘቱን አሜሪካ ይፋ ብታደርግም ሃገሪቱ በጉዳዩ ዙሪያ የሰጠቸው ምላሽ አለመኖሩን ቴሌግራፍ የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።

በሃሰተኛ ኤምባሲው ላይ በተካሄደ ወረራ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ የአሜሪካ ባለስልጣናት ቁጥሩን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።