በጋቦን የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ተደረገ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 30/2011)በማዕከላዊ አፍሪካ ክፍል በምትገኘው ጋቦን የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ያደረጉት ሁለት ወታደሮች ሲገደሉ 3ቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘገበ።

ከግልበጣው ሙከራ ጀርባ አሉ ተብለው በተጠረጠሩ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና የሲቪል ድርጅት ሃላፊዎች ላይ ምርመራ እንደሚካሄድም የጋቦን መንግስት አስታውቋል።

ጋቦን

እሁድ ሌሊት 10 ሰዓት ተኩል ላይ የሃገሪቱን የሬዲዮና የቴሌቭዥን ጣቢያዎች በመቆጣጠር ለግማሽ ክፍለ ዘመን የዘለቀው የቦንጎ ቤተሰብ አገዛዝ ማብቃቱን የገለጹት ወታደሮች የሬዲዮ ጣቢያውንም ብዙ ማይቆዩበት ቤተመንግስትም ሳይደርሱ ሙከራቸው ከሽፏል።

በነዳጅ ሃብት የበለጸገችውና 2 ሚሊየን ያህል ህዝብ ብቻ የሚኖርባት ጋቦን በማዕከላዊው የአፍሪካ ክፍል የምትገኘውና እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር እስከ 1960 በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ውስጥ የቆየች ሃገር ነች።

ነጻነቷን ካገኘችበት 1960 ወዲህ የአሁኑን ፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎንና የቀደሙትን አባታቸውን ኦማር ቦንጎን ጨምሮ ሶስት መሪዎችን አይታለች።

ከአፍሪካ ሃገራት ሃብታም ተብለው ከሚጠቀሱት ጥቂት ሃገራት አንዷ የሆነችውና በሰብዓዊ ልማት ደረጃ በተባበሩት መንግስታት መስፈርት ከሰብ ሰሃራ አፍሪካ ሃገራት 4ኛ የሆነችው ጋቦን በነፍስ ወከፍ ገቢ ደረጃም 5ኛውን ስፍራ ይዛለች።

ይህች በነዳጅ ሃብት የበለጸገችውና በአንድ ቤተሰብ አገዛዝ ግማሽ ክፍለ ዘመን የቆየችው ጋቦን ሃብታም ብትሆንም ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ባለመኖሩ ብዙ ድሆች ከነድህነታቸው በጉስቁልና ይኖሩበታል።

የጋቦንን መንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን ተቆጣጥረው የነበሩት በመቶ አለቃ ኬሊ ኢንዶ ኦብያንግ የሚመሩት የግልበጣ ሙከራው ተሳታፊዎች የአንድ ቤተሰብን አገዛዝ ለማብቃት እና ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ መነሳታቸውን እንዲሁም የሃብት ክፍፍልን ፍትሃዊ ለማድረግ መንቀሳቀሳቸውን ገልጸው ነበር። በነበር ቀረ እንጂ።

ጋቦን ከነጻነት ወዲህ የተሞከረባት የግልበጣ ሙከራ ይኽ ሁከተኛው ሲሆን የመጀመሪያውም ከ50 ዓመታት በፊት ተሞክሮ ከሽፏል።

የመጀመሪያው የጋቦን ፕሬዝዳንት ገብርኤል ሊዮን ሜባ እ/ኤ/አ ነሃሴ 17/1960 ከፈረንሳይ ነጻ የወጣችውን ጋቦንን የመሪነት መንበረ በተረከቡ በአራተኛው ዓመት እ/ኤ/አ በየካቲት 1964 የተካሄደባቸው የግልበጣ ሙከራ ቢከሽፍም ከሶስት ዓመት በኋላ በተፈጥሮ ሞት ተሸንፈው ስልጣናቸውን ለቀዋል።

በወቅቱ የሃገሪቱ ም/ፕሬዝዳንት የነበሩት የአየር ሃይሉ ካፒቴን ኦማር ቦንጎ እ/ኤ/አ ከ1967 እስከ 2009 ለ42 ዓመታት በስልጣን ላይ ቆይተው በሞት ተሸንፈው በ73 ዓመታቸው ስልጣናቸውን ሲለቁ ከ30 በላይ ከሚሆኑት ልጆቻቸው አንዱ የሆኑት የ60 ዓመቱ አሊ ቦንጎ የመሪነቱን ስልጣን ተረከቡ።

ስልጣን ሲይዙ 50 ዓመታቸው የነበሩት አሊ ቦንጎ በአባታቸው የስልጣን ዘመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል። ከ10 ዓመታት የስልጣን ዘመን በኋላ የተቃጣባቸውም ሙከራ ከሽፏል።