በጋምቤላ 17 ሰዎች ተገደሉ ሶስት ሴቶች ተጠለፉ

መጋቢት 4 ቀን 2004 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-የጋምቤላ የኢሳት ምንጮች በፎቶ ግራፍ አስደግፈው በላኩት መረጃ ተማሪዎቹ የእረፍት ጊዜያቸውን ጨርሰው  በመጪው ሰኞ በሚጀመረው ትምህርት ላይ ለመገኘት ከጎደሬ ተነስተው ወደ ጋምቤላ ኮሌጅ በማምራት ላይ ነበሩ።

ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ጀዊ ከተማ ላይ የፌደራል ልዩ ሀይል ልብስ የለበሱት ታጣቂዎች ተማሪዎችን ከአውቶቡሱ እንዲወርዱ አዘው  ያላቸውን ሁሉ ንብረት እንዲያስረክቡ ጠይቀዋል።

ጥቂት ቆይቶም ተማሪዎቹ በሆዳቸው እንዲተኙ ታዘዋል። ታጣቂዎቹ መረሸን ሲጀምሩ የተወሰኑት የሞት ሽረታቸውን ለማምለጥ ሙከራ አድረገዋል። ይሁን እንጅ 17 ተማሪዎች ህይወታቸው አልፎአል። 8 ተማሪዎች በጽኑ ቆስለው ተርፈዋል፤ 6ቱ ደግሞ አምልጠዋል። ካመለጡት መካከል ሹፌሩን ጨምሮ አንዲት እናት የሚገኙበት ሲሆን ፣ ልጃቸው በጽኑ ቆስላ መትረፉዋ ታውቋል።

ታጣቂዎቹ 6 ሴቶችን የወሰዱ ሲሆን 3ቱን ወዲያውኑ ለቀዋቸዋል።

ዘግይቶ ወደ አካባቢው የደረሰው ልዩ የፌደራል ፖሊስ ሀይል ተመሳሳይ ልብስ በለበሱት ታጣቂዎች መመታቱም ታውቋል። ምን ያክል የፌደራል ፖሊስ አባላት እንደተመቱ ለማወቅ ባንችልም፣ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ግን ለማወቅ ተችሎአል። የፌደራል ፖሊስ አባላት መከላከያ አስቀድሞ በቦታው ቢደርስ ኖሮ ታጣቂዎችን ለመያዝ ይቻል ነበር፣ ይሁን እንጅ ፌደራል ፖሊስ ፈጥኖ በመድረሱ እና ታጣቂዎቹ የፉደራል ፖሊስ ልብስ የለበሱ በመሆናቸው መለየት ሳይቻል ቀርቶ ለጉዳት ተዳርገናል በማለት መናገራቸውን ለማወቅ ተችሎአል።

አብዛኞቹ ማቾችና ቁስለኞች የጎደሬና የቴፒ ልጆች ናቸው። በጋምቤላ ሆስፒታል ውስጥ አስከሬኖች በየቦታው ወዳድቀው እንደሚታዩ፣ የተማሪዎቹ ወላጆች ሆስፒታሉን ከበው ልጆቻቸውን ለመውሰድ በመጠባበቅ ላይ ናቸው።ቁስለኞቹ ጉልኮስ የተተከለላቸው ቢሆንም ትናንት መብራት በመጥፋቱ ምክንያት በቂ ህክምና አንዳላገኙ ታውቋል።

የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ኦሞድ ኦባንግ ትናንት ከምሽቱ 12 ተኩል ላይ የጋምቤላን ሆስፒታል ከጎበኙ በሁዋላ አስከሬኖቹ ወጥተው ለቤተሰቦቻቸው እንዳይሰጡ አዘዋል። ፕሬዚዳንቱ ይህን ትእዛዝ ለምን እንደሰጡ አልታወቀም።

በጋምቤላ ካለፉት 2 ወራት ጀምሮ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በሚፈጽሙት ጥቃት አለመረጋጋቱ እየጨመረ ነው። ከአንድ መንደር ወደ ሌላ መንደር ያለ ፖሊስ አጀብ መጓዝ በፍጸሙን አይቻልም። የመንግስት ሰራተኞች ከቢሮ ወደ ቢሮ ለመሄድ እንኳ በእጅጉ እየፈሩ ነው።

ከዚህ ቀደም  በሰላም አውቶብስ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በሁዋላ ፣ ተመሳሳይ ጥቃት ሲፈጸም የትናንትናው የመጀመሪያ ነው።

ይሁን እንጅ ሰሞኑን በደረሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች በ20 ዎቹ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። መንግስት በጋምቤላ ስለተፈጸመው ጥቃት እስካሁን ያለው ነገር የለም።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide