ኢሳት (ሚያዚያ 11 ፥ 2008)
ከቀናት በፊት በጋምቤላ ክልል የተፈጸመውን የታጣቂዎች ጥቃት ተከትሎ ከ20ሺ በላይ ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፈናቀሉ።
እነዚሁ ነዋሪዎች በኑዌር ዞን በማላዌ፣ በጅካዎና በላሬ ወረዳዎች በሚገኙት ሶስት ወረዳዎች መፈናቀላቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጋትሉዊክ ቱት ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙና ይፋ አድርገዋል።
ከሶስቱ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ ወደተለያዩ አጎራባች አካባቢዎች ተወስደው የሚገኙ ሲሆን የክልሉ ካቢኔም ማክሰኞ የአስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱ ታውቋል።
የሙሩሌ ታጣቂዎች በኑዌርና በአኝዋክ ዞኖች ድንበር አካባቢዎች በተደጋጋሚ ጥቃት እየፈጸሙ በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ሲያደርሱ መቆየታቸውንም የክልሉ ባለስልጣናት በመግለጽ ላይ ናቸው።
ከቀያቸው ተፈናቅለው የሚገኙ ከ20ሺ በላይ ሰዎችንም ለማረጋጋትና ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የፌዴራል መንግስት በበኩሉ ጥቃቱን ፈጽመዋል የተባሉ ታጣቂዎች ላይ እርምጃን ለመውሰድ በድንበር ዙሪያ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ማክሰኞ በድጋሚ ገልጸዋል።
ይሁንና ድንበር ዘልቆ ጥቃት ለመፈጸም ከደቡብ ሱዳን መንግስት ፍቃድ እየተጠበቀ እንደሆነ አክለው አስታውቀዋል።
የደቡብ ሱዳን መንግስት የሙርሌ ታጣቂዎችን በተለያዩ ጊዜያት ትጥቅ ለማስፈታት ሙከራ ቢያደርግም ያልተሳካለት ሲሆን በጆግሌ ግዛት የሚገኙት እነዚሁ ታጣቂዎች በአካባቢው ጠንካራ ይዞታ እንዳላቸውም የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።