በጋምቤላ ግጭቱ ተባብሶ ቀጥሏል ተባለ

ኢሳት (ሚያዚያ 17 ፥ 2008)

በጋምቤላ ክልል በሚገኙ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች መካከል በተቀሰቀሰ የጎሳ ግጭት በትንሹ 14 ሰዎች መገደላቸውንና ግጭቱ በመባባስ ላይ መሆኑን አለም አቀፉ የእርዳታ ተቋማት ገለጡ።

አንድ የግብረሰናይ ድርጅት ተሽከርካሪ ሁለት የኑዌር ጎሳ ተወላጆችን ገጭቶ በመግደሉ በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ አለመረጋጋት መፍጠሩንና ድርጊቱ ወደጎሳ ግጭት ማቅናቱን የተለያዩ አካላት ይፋ አድርገዋል።

የህጻናቱን መገደል ተከትሎም በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች 10 ኢትዮጵያውያንን ገድለው የነበረ ሲሆን፣ የፀጥታ ሃይሎችም ከድርጊቱ ጋር እጃቸው አለበት የተባሉ 30 ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ታውቋል።

ባለፈው ሳምንት የተቀሰቀሰው ይኸው ግጭት በሳምንቱ መገባደጃ ቅዳሜና እሁድም ቀጥሎ በትንሹ 14 ሰዎች መገደላቸው አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የተለያዩ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ ሰኞ ዘግቧል።

በአኝዋክ እና በኑዌር ጎሳዎች መካከል ተቀስቅሶ የሚገኘው ይኸው ግጭት እየተባባሰ መሄዱን የሚገልጹት የእርዳታ ተቋማት የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የፈረንሳዩ ድንበር የለሽ ግብረሰናይ ተቋም የዚሁ ጥቃት ኢላማ መሆናቸውንም ለመረዳት ተችሏል።

የአኝዋክ ጎሳ አባላት እነዚህ ድርጅቶች የኑዌር ተወላጆችን ይደግፋሉ በሚል ተቃውሞ እያካሄዱ የሚገኝ ሲሆን፣ ግጭቱ ተባብሶ በመሄድ የበለጠ አደጋን ያስከትላል ተብሎም ተሰግቷል።

ንብረትነታቸው የፈረንሳዩ ግብረ ሰናይ ድርጅት የሆኑ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ንብረቶችም ውድመት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ስደተኞችም ከአካባቢው በመሸሽ በሆቴሎች ተጠልለው እንደሚገኙ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው አመልክቷል።

በቅርቡ በደቡብ ሱዳን የተቀሰቀሰው ግጭት ተከትሎ አብዛኞቹ ንዌር ስደተኞች በጋምቤላ ክልል መሰደዳቸው የሚታወስ ነው።

ባለፈው ሳምንት በጋምቤላ ክልል የተፈጸመ ጥቃት በክልሉ አለመረጋጋት እንዲሰፍን አድርጎ እንደሚገኝም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

በዚሁ ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለው የነበረ ሲሆን፣ ወደ 20ሺ የሚጠጉ ነዋሪዎችም ከቀያቸው ተፈናቅለው ይገኛሉ።