በጋምቤላ የደረሰን ጥቃት ተከትሎ ኢትዮጵያ አንድ የልዑክ ቡድን ወደ ደቡብ ሱዳን ላከች

ኢሳት (መጋቢት 8 ፥ 2009)

ሰሞኑን በደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ኢትዮጵያ የልዑኩ ቡድን ወደ ደቡብ ሱዳን መላኳን የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አርብ አስታወቀ።

የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት ማዊን ሚሎል የሃገሪቱ የቦማ ግዛት የብሄራዊ መንግስቱ ታጣቂዎቹ ወደ ጋምቤላ ክልል ሰርገው በመግባት በሰዎች ላይ ግድያና አፈና መፈጸማቸውን ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ይህም ሆኖ ግን የግዛቲቱ ባለስልጣናት በታጣቂ ሃይሎች ጥቃት ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ የታወቀ ነገር አለመኖሩን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በሳምንቱ መገባደጃ በሁለት የጋምቤላ ክልል አካባቢዎች በፈጸሙት ጥቃት በትንሹ 28 ሰዎች ተገድለው ወደ 43 ህጻናት ደግሞ ታግተው መወሰዳቸው የጋምቤላ ክልል ባለስልጣናት ሲገልጹ ቆይቷል። ወደ 1ሺ የሚሆኑት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ግን ስለፈጸሙት ጥቃትና ስላደረሱት ጉዳት እስከአሁን ድረስ የሰጡት መረጃ የለም።

ወደ ደቡብ ሱዳን የተጓዙ የኢትዮጵያ ህጻናት በሚለቀቁበት ጉዳይ ላይ ከሃገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፈው አመት በክልሉ በተመሳሳይ መልኩ በሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ኢትዮጵያ ወደ ጁባ ተወካዮችን በመላክ በደቡብ ሱዳን መንግስት በኩል ታጣቂው ጋር ድርድር ማካሄዷ ይታወሳል። ለሳምንታት ሲካሄድ የቆየውን ይህንኑ ድርድር ተከትሎ ታግተው ከተወሰዱ ከ120 ህጻናት መካከል ወደ 80 የሚሆኑት በሶስት ዙሮች መለቀቃቸው በወቅቱ ሲገለጽ ቆይቷል።

በደቡብ ሱዳን የሚገኙ የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች ህጻናቱን ለማስለቀቅ በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ ምክክርን እንደሚያካሄዱ ራዲዮ ታማዙጂ ከሃገሪቱ ዘግቧል።

ጎግ እና ጆር ተብለው በሚጠሩ የጋምቤላ ክልል በተፈጸመው ጥቃት ግድያ ከተፈጸመባቸው ነዋሪዎች በተጨማሪ የንብረት ዘረፋ መፈጸሙንም ታውቋል። የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት በፈጸሙት ጥቃት ከ130 በላይ ሰዎች ተገድለው ወደ 125 ህጻናት ታግተው መወሰዳቸው የሚታወስ ነው።

በወቅቱ ተፈጽሞ በነበረው ጥቃት ከ20ሺ በላይ ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳትም መወሰዳቸውን ነዋሪዎች ሲገልጹ ቆይተዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በአካባቢው ያለውን ጥቃት ለማስቆም ድልድይን ጨምሮ የመሰረተ-ልማት ስራ እንዲከናወን ከቀናት በፊት ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን መናገራቸው ይታወሳል።