ነሃሴ ፲፩ ( አሥራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያ በመካሄድ ላይ ካለው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ 21 የኦሮሞ ተወላጅ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮች ሃምሌ 30 ቀን 2008 ዓም መታሰራቸውን ኢሳት ዘግቦ ነበር። አማኞቹ ከጥምቀት ቦታ እየዘመሩ ወደ ቤተክርስቲያናቸው እየሄዱ ሳለ፣ የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት ዝማሬው የተቃውሞ መስሎአቸው ሁሉንም ካገቱ በሁዋላ እየደበደቡ አስረዋቸዋል። ምእመናኑ ሲዘምሩ የነበረው የምስጋና የአምልኮ መዝሙር እንደነበር የገለጹት የቤተክርስቲያኑዋ አባል፣ እስረኞቹ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በስቃይ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በዚሁ እለት የኦሮሞ የነጻነት አርማ በጋምቤላ ከተማ ተሰቅሎ ተገኝቷል በሚል በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች ታስረዋል። አርማው የተሰቀለው በክልሉ መስተዳደር ጽ/ቤት ውስጥ ነው። ምንጮች እንደገለጹት አርማው ሆን ተብሎ በቅንብር በመስተዳድሩ ጽ/ቤት ላይ እንዲሰቀል የተደረገው በክልሉ የሚኖሩ የኦሮሞ ወጣቶችን ለማሰር ነው።