ኢሳት (የካቲት 25 ፥ 2008)
በጋምቤላ ክልል የእርሻ መሬቶችን የተረከቡ ወደ 100 አካባቢ ባለሃብቶች ክልሉ መሬቱን የሰጣችሁ በስህተት ነው በሚል መሬታቸውን እንዲመልሱ ተወሰነ።
ባለሃብቶቹ በበኩላቸው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በማፍሰስ በህጋዊ መንገድ ወደስራ መግባታቸውንና የተሰጣቸው ማሳሰቢያ ቅሬታን እንዳሳሰረባቸው በመግለጽ ላይ መሆናቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የፌዴራልና የክልሉ መንግስት ተናበው ባለመስራታቸው ችግሩ መፈጠሩን የሚናገሩት ባለሃብቶቹ፣ ከስድስት አመት በፊት መሬቱን በህጋዊ መንገድ ከክልሉ መንግስት መረከባቸውንም አስታውቀዋል።
ይሁንና፣ ክልሉ በፌዴራል መንግስት ስር የሚተዳደር መሬት በስህተት ነው የሰጣችሁ ተብለው የተረከቡትን በሺዎች የሚቆጠር ሄክታር መሬት እንዲያስረክቡ ተጠይቀዋል።
የእርሻ ልማትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ በበኩሉ በጋምቤላ ክልል ስር የሚገኙ የወረዳ ባለስልጣናት መሬቱ አሁንም ድረስ በህገወጥ መንገድ የተሰጠ ነው ሲሉ ምላሽን ሰጥተዋል።
ቅሬታን እያቀረበ ያሉት ባለሃብቶች የተሰጣቸውን መሬት በማን ስር የሚተዳደር ስለመሆኑ እውቀቱ እንደሌላቸው ችግሩ የፌዴራልና የክልሉ መንግስት መሆኑን ገልጸዋል።
ስማቸውን መገለጽ ያልፈለጉት ባለሃብቶች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብን በማውጣት የተረከቡትን የእርሻ መሬቶች ለመመንጠርና ሌሎች ግንባታዎችን ለማካሄድ እንዳዋሉ በመግለፅ መንግስት ለደረሰባቸው ኪሳራ ካሳ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
ባለሃብቶቹ እንዲመልሱ የተጠየቁት በሺዎች ሄክታር የሚቆጠር መሬትም በአሁኑ ሰዓት በጸጥታ ሃይሎች ጥበቃ እየተደረገበት እንደሚገኝ ታውቋል።
መሬታቸውን እንዲያስረክቡ የተጠየቁት ወደ 100 አካባቢ ባለሃብቶችም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ መፍትሄውን እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ደብዳቤን ያስገቡ ሲሆን የመጨረሻ ምላሽ እስኪሰጣቸው ድረስም ንብረቶቻቸውን ከመሬታቸው ላይ እንደማያነሱ አስታውቀዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የተጠየቁት የክልሉ ፕሬዚደንት ጋትሉአክ ቱት-ኮን በበኩላቸው ምንም አይነት ምላሽን እንደማይሰጡ ገልጸው የፌዴራሉ መንግስት ዝርዝር መረጃን ይስጥ ሲሉ ለሪፖርተር ጋዜጣ ተናግረዋል።
ይህ እርምጃ በአብዛኛው የጋምቤላን መሬት የተቆጣጠሩት በቀድሞ የህወሃት ታጋዮችና ሌሎች የትግራይ ተወላጆችን ይጨምር እንደሆን የታወቀ ነገር የለም።
በጋምቤላ ክልል ነዋሪውን በማፈናቀል በተደለደለው ሰፋፊ የእርሻ መሬት የትግራይ ተወላጆች የ70 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን የኦክላንድ ኢንስቲቲዩት ማጋለጡ ይታወሳል።