ኢሳት (ኅዳር 16 ፥ 2009)
በጋምቤላ ክልል በህገወጥ መንገድ የሃገሪቱን የአየር ክልል ጥሳችሁ ገብታችኋል ተብለው በቁጥጥር ስር የነበሩ የተለያዩ ሃገራት ፓይለቶች የመንግስት ፈቃድ ተሰጥቷቸው እንደነበር ይፋ አደረጉ።
በውድድር ላይ የነበሩት እነዚሁ ከ40 የሚበልጡ ፓይለቶች የኢትዮጵያ አቪየሽን ባለስልጣን ሊያደርጉ ለነበረው የአውሮፕላን በረራ ፈቃድ ሰጥቷቸው እንደነበር መግለጻቸውን ዴይሊ ሜይል የተሰኘ የብሪታኒያ ጋዜጣ ዘግቧል።
ይሁንና ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለፓይለቶቹ ቡድን ፈቃድን ከሰጠ በኋላ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፓይለቶቹ ውድድራቸውን ከሱዳን ከጀመሩ በኋላ ፈቃዳቸውን እንደሰረዘባቸው አስታውቀዋል።
ሚኒስትሩ ፈቃዳቸውን በምን ምክንያት ሊሰርዝባቸው እንደቻለ ግልጽ እንዳልሆነላቸው የሚናገሩት ፓይለቶች፣ በጋምቤላ ክልል በቁጥጥር ስር በነበሩ ጊዜ በደረቅ የሲሚንቶ ወለል ላይ እንዲተኙ ተገደው እንደነበርም ቅሬታቸውን ለጋዜጣው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን 25 በሚሆኑ መለስተኛ አውሮፕላኖች ይጓዙ የነበሩ ፓይለቶች በህገወጥ መንገድ ወደ ሃገር በመግባታቸው ሳቢያ ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሆነ ሃሙስ መግለጹ ይታወሳል።
የተለያዩ ሃገራት ዜጎችን ያካተተው የፓይለቶች ቡድን በምን ምክንያት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፈቃዳቸው ሊሰረዝባቸው እንደቻለ ከመንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።
በረራችንን ከጀመርን በኋላ ፈቃዱ ስለመሰረዙ መረጃ ቢደርሰንም ወደ ሱዳን የሚመልሰን ነዳጅ ባለመኖሩ ጉዞአችንን ለመቀጠል ተገደን ነበር ሲል አንድ የፓይለቶቹ ቡድን አባል ለዴይሊ ሜይል ጋዜጣ አስረድቷል።
ፓይለቶቹ ከሁለት ቀን እገታ በኋላ ሃሙስ ከጋምቤላ ክልል እንዲወጡ ተፈቅዶላቸው ወደ ሆቴል እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን፣ የቡድኑ አባላት ዛሬ አርብ ጉዞአቸውን ወደ ኬንያ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በጋምቤላ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ የሁለት ቀን ቆይታ የነበራቸው የፓይለቶች አባላት በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በሲሚንቶ ወለል ላይ እንዲተኙ ተገደው እንደነበር ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
የሙቀት መጠኑ 104 ፋራናይት በሆነበት አካባቢ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር እንኳን ሳይሰጠን ወለል ላይ እንድንተኛ በጸጥታ ሃይሎች ተገደን ነበር ሲሉ ፓይለቶቹ ለዴይሊ ሜይል ጋዜጣ አስረድተዋል።
የቡድኑ አባላት በቆይታቸው የእጅ ስልኮቻቸውና ኮምፒውተሮቻቸው ተወስዶባቸው እንደነበርም የገለጹ ሲሆን የውድድሩ አዘጋጅ የሆነው ቪንቴጅ ኤይር ራሊ በበኩሉ ፓይለቶቹ በቁጥጥር ስር የዋሉበት ምክንያት ግልፅ እንዳልሆነለት በድረገጹ ባሰፈረው ጹሁፍ አመልክቷል።
ወደ 40 የሚጠጉትና ከተለያዩ ሃገራት የተውጣቱት የፓይለቶቹ ቡድን 10 የአፍሪካ ሃገራትን በሚሸፍን የአውሮፕላን የውድድር ጉዞ ላይ እንደነበሩ ከአዘጋጆቹ ለመረዳት ተችሏል።