ኢሳት (ሚያዚያ 21 ፥ 2008)
በቅርቡ በጋምቤላ ክልል በተፈጸመው ጥቃት ከባድ የመሳሪያ ጉዳይ የደረሰባቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደጎረቤት ደቡብ ሱዳን መሸሻቸውንና የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር አርብ ይፋ አደረገ።
እነዚሁ በማይውት ግዛት ህክምና እየተደረገላቸው የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው 39 ሲሆን ስደተኞቹ በጦር መሳሪያ ተኩስ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው እንደሆነም ታውቋል።
ከባድ የህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው ከሚገኙት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተጨማሪ ሌሎች ተጎጂዎች ማይውት ወደሚገኘው የቀይ መስቀል የጤና ማዕከል እየመጡ መሆኑን በደቡብ ሱዳን የማይውት አስተዳደር ሆስፒታል ሃላፊ የሆኑት ቺዩኪ ዮሺዳ ገልጸዋል።
በአካባቢው የህክምና መስጫ ጣቢያ ባለመኖሩ ምክንያትም የማይውት ሆስፒታል ከአቅሙ በላይ ተጨናንቆ እንደሚገኝም የሆስፒታሉ ሃላፊ አክለው አስታውቀዋል።
ወደ80 ሺ ህዝብ በሚኖርባት የማይውት አስተዳደር የሚገኘው ይኸው ሆስፒታል በድርቅ አደጋ ለተጎዱ ሰዎች አገልግሎትን ደርቦ የሚሰጥ በመሆኑም ከአቅም በላይ የሆነ መጨናነቅ መፍጠሩን የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር አክሎ ገልጿል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በጋምቤላ ክልል በተፈጸመው በዚሁ ጥቃት ከ200 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከ100 የሚበልጡ ህጻናትም ታፍነው ተወስደዋል።
መቀመጫቸውን በጎረቤት ሱዳን ያደረጉ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ጥቃቱን እንደፈጸሙ ያስታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት ወደ 100 የሚጠጉ ሰዎችም ጉዳት እንደደረሰባቸው በወቅቱ ገልጿዋል።
ከሞቱትና ጉዳት ከደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን በተጨማሪም ከ20ሺ የሚበልጡ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን ድርጊቱ በክልሉ አለመረጋጋትን ፈጥሮ እንደሚገኝም ታውቋል።
መንግስት ህጻናቱን አፍነው ወስደዋል ያላቸው ታጣቂዎች ያሉበት ስፍራ መታወቁን በተደጋጋሚ ይፋ ቢያደርግም እስከአሁን ድረስ የተወሰደ እርምጃ ስለመኖሩ የተሰጠ መረጃ የለም።
ይሁንና የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ባለስጣናት ህጻናቱን ለማስለቀቅ ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር ምክክር እየተካሄደ መሆኑን ሃሙስ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ አምባሳደሮችና የውጭ ሃገር ተወካዮች መግለጻቸው ይታወሳል።
የደቡብ ሱዳን መንግስት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች መሳሪያ (ትጥቅ) ለማስፈታት በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ ቢቆይም ሳይሳካለት መቅረቱን የሃገሪቱ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።
የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ አመራሮችም ከጥቃቱ ጀርባ የማን እጅ አለበት በሚለው ዙሪያ ውዝግብ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ግን የሃገሪቱ መንግስትም ሆነ የአማጺ ቡድኖች ከጥቃቱ ጀርባ እጃቸው የለበትም ሲል በተደጋጋሚ አስታውቋል።