በጋምቤላ የሰዎች መገደልና መታፈን አዲስ አይደለም ሲሉ የክልሉ ፕሬዚደንት አስታወቁ

ኢሳት (ሚያዚያ 12 ፥ 2008)

በድንበር ዘለል የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ጥቃት ኢትዮጵያ ግዛት ገብተው ሰዎች ሲገድሉም ሆነ ታፍነው ሲወስዱ ይህ የመጀመሪያቸው አለመሆኑን የጋምቤላ ክልል ፕሬዚደንት ገለጹ። ከሰሞኑ ጥቃት በፊት ባሉት 20 ቀናት ብቻ ታጣቂዎቹ 21 ኢትዮጵያውያን ገድለው፣ 17 ህጻናትን አፍነው መውሰዳቸውን ለመንግታዊና ለፓርቲ ሚዲያዎች በሰጡት ቃለምልልስ አመልክተዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ እንደተናገሩት አርብ ሚያዚያ 8 ፥ 2008 ከተገደሉት 182 ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ፣ ከመጋቢት 15 እስከ ሚያዚያ 6 ፥ 2008 26 ሰዎች በተመሳሳይ መገደላቸውን እንዲሁም 21 ህጻናት ታፍነው መወሰዳቸውም አብራርተዋል። ጥቃቱ ከመጋቢት 15 ጀምሮ ሲቀጥል የክልሉ መንግስትም ሆነ የፌዴራል መንግስት ዜጎችን ለመታደግ ለምን እንዳልተንቀሳቀሱ ምላሽ አልሰጡም ብለዋል።

ባለፈው አርብ ሚያዚያ 8 ፥ 2008 የተገደሉት ደግሞ 182 መሆናቸውን አስረድተዋል። ቆስለው ሆስፒታል ከገቡት ሁለቱ መሞታቸውን እንዲሁ ስድስቱ ደግሞ ለከፍተኛ ህክምና ወደጅማ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የጋምቤላው ክልል ፕሬዚደንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት አብራርተዋል። እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ማብራሪያ በሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሆስፒታል ውስጥ የሞቱትን ጨምሮ 210 ሰዎች ተገድለዋል።

ታፍነው የተወሰዱት ህጻናት ለማስመለስ የሚደደረገውን ጥረት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ በግዛታቸው ውስጥ አሰሳ እየተደረገ ነው በማለት የተጨበጠ ነገር አለመታየቱን አስረድተዋል።