ሰኔ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የጋምቤላ ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት በጋምቤላ እርሻ ስራ ተሰማርተው የሚፈለግባቸውን የመሬት ኪራይ እዳ ባልከፈሉ 150 ባለሀብቶች ላይ ያወጣው የማሳሰቢያ ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፤ የጋምቤላን መሬት የተቀራመቱት ከ90 በመቶ የሚልቁት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የትግራይ ተወላጆች ናቸው።
ባለሀብቶቹ ከ2006 እስከ 2007 ሰኔ ወር ድረስ ያለባቸውን ውዝፍ እዳ አጠቃለው እንዲከፍሉ በወጣው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ላይ ስማቸው በዝርዝር ተቀምጧል።
ቢሮው በማስጠንቀቂያ ደብዳቤው ባለሀብቶቹ ከ2006 -2007 ዓም ያለባቸውን የመሬት መጠቀሚያ ኪራይ እስከ ሰኔ 15/2007 ዓም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ አጠቃለው ካልከፈሉ እርምጃ በመውሰድ ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል እንደሚያሳውቅ ገልጿል።
አንድ ሁልት ተብለው በጣት ከሚቆጠሩት የሌላ ብሄር ተወላጆች በስተቀር አብዛኞቹ የአንድ አካባቢ ተወላጅ መሆናቸው ማስታወቂያውን ከስም ዝርዝራቸው በማየት ለማረጋገጥ ይቻላል። የተጠቀሱት ባለሃብቶች የህወሀት አባላት ይሁኑ ወይም አይሁኑ በደብዳቤው ላይ ባይጠቀስም ከዚህ ቀደም የክልሉ መሬት በህወሃት አባላት ቁጥጥር ስር መዋሉን በተመለከተ የሚቀርቡ ዘገባዎችን እውነትነት ያረጋገጠ ሆኗል።
ተወላጆች በሃይል ከቀያቸው እየተፈናቀሉ መሬቱ ለገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች መሰጠቱ በክልሉ ለሚታየው ተደጋጋሚ ግጭትና አለመረጋጋት ዋና መንስኤ መሆኑ ሲዘገብ ቆይቷል።