ኢሳት (ታህሳስ 25 ፥ 2007)
የጋምቤላ ልዩ ሃይል አባላት ከእነሙሉ ትጥቃቸው የህወሃትን መንግስት በመክዳት ተቃዋሚዎችን መቀላቀላቸው ከአገር ቤት የደረሰን ዜና አመለከተ።
የልዩ ሃይል አባላቱ የታጠቁትን የጦር መሳሪያ በመያዝ የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ጥምረት ግንባር የተባለው ሸማቂ ቡድን መቀላቀላቸውየኢሳት ምንጮች ከአገር ቤት ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ብዛት ያላቸው የስርዓቱ መከላከያ ሃይል አባላት ስርዓቱን እየከዱ ሸማቂ ቡድኑን እየተቀላቀሉ ናቸው ተብሏል።
የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ጥምረት ግንባር ሊቀመንበር አቶ አቡላ ኦባንግ አሁን የተቀላቀሏቸው የልዩ ሃይል አባላት ለትግሉ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉ ለኢሳት ተናግረዋል።
አቶ አቡላ የልዩ ሃይል አባላት ስምና የማዕረግ ደረጃ ለራሳቸው ለልዩ ሃይል አባላትና ለቤተሰቦቻቸውና ደህንነት ሲባል ከመግለጽ ተቆጥበው፥ የጋምቤላ ክልላዊ መንግስትም ወደአካባቢው ወታደር በመላክ ከፍተኛ አሰሳ እያደረገ መሆኑ አስረድተዋል። የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራዊያዊ ጥምረት ግንባር አሁን በኦሮሚያ የተከሰተውን ህዝባዊ እምቢተኝነት በሌሎችም ክልሎች ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፏል። ጥምረቱ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተጀመረውን ህዝባዊ ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም የለውጥ ሃይሎችም ይህንን እድል በመጠቀም በአንድነት እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ጥምረት እና የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ንቅናቄ የጀመሩትን ትግል በቁርጠኝነት ለማካሄድ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ጋር በመሆን የጋራ የትግል ስምምነቶን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰናቸውን በቅርቡ ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።
የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ጥምረት ገዢው የህወሃት/የኢህአዴግ መንግስት በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ በርካታ ከተሞች የፈጸሙውን ግድያ በማውገዝ ከኦሮሞ ህዝብ ጎን እንደሚቆም ባወጣው መግለጫ አመልክቶ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም፣ ገዢው መንግስት በቅርቡ ከሱዳን ጋር ድንበር ለማካለል የደረገው ስምምነትም ተቀባይነት የሌለውና የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ እንደሆነ ጥምረቱ አክሎ ገልጾ ነበር።